Search

በመዲናዋ 29 አባወራዎችን ከመኖሪያቸው እንዲነሱ ያደረገው የመሬት መንሸራተት አደጋ

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 38

በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ብርጭቆ ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው  አካባቢ የመሬት መሰንጠቅና መንሸራተት ማጋጠሙን ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር ነበር፡፡

ኢቢሲ ዶትስትሪም ጉዳዩን አስመልክቶ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

 

ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በማብራሪያቸውም፤ ነሀሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ ባለው አስፓልት ላይ የመሬት መሰንጠቅ ምልክት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም 4 ሺህ 242 አባወራዎች የሚኖሩ ሲሆን፤ በዚህ ግቢ ውስጥ ካሉ ብዛት ያላቸው ህንፃዎች የሚወጣው የውኃ ፍሳሽ፤ የዝናብ ውኃ ታሳቢ ያላደረገ የውኃ ፍሳሽ የግንባታ ችግር እንደነበረበት ተናግረዋል።

በኮንዶሚኒየሞቹ ዙሪያ ያሉ የጎርፍ ማፍሰሻ ቱቦዎች በተለያየ ቆሻሻ የተደፈኑ በመሆናቸው ውኃው ወደ ወንዙ እንዳይሄድ እንዳደረገውም ነው ያነሱት፡፡

እነዚህ ችግሮች እንዳሉ ሆነው በሌላ በኩል ክረምቱን ተከትሎ የመጣው ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተት አደጋው እንዲከሰት ማድረጉን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢኒስቲትዩት ባደረገው ጥናት መረጋገጡን ኢንጂነር ወንድሙ ገልፀዋል፡፡ 

በዋናነት ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም በሚገነባበት ወቅት ከስፍራው የሚወጣው አፈር የሚወገደው አቅራቢያው ባለ ወንዝ እንደነበረ ጠቅሰው፤ ወንዙም ከአፈር ጋር የተደባለቀ ውኃ እንዲያቁር ስለማድረጉም አመልክተዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በሚገኙ ሚኪሊላድ ትምህርት ቤት አጥር ላይ፣ እቃ ማከማቻ ጊዜያዊ መጋዘን እንዲሁም የምገባ ማዕከል ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ነው የገለጹት፡፡ 

በጋራ መኖሪያ ቤት ብሎክ 13 ህንጻ ላይ ጉዳት ባይከሰትም የህንጻው ዙሪያውን የመሸሽ ሁኔታ እንዳጋጠመ አክለዋል፡፡

በወረዳ 14 ባለ የእምነት ተቋም ቢሮዎች፣ በቅጥር ጊቢው ባለ መዋእለ ህጻናት የመማሪያ ክፍሎች እና መጸዳጃ ላይ ጉዳት እንዳደረሰም ጠቅሰዋል፡፡

የአደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች የመለየት ስራ እየሰሩ እንዳለ የገለጹት ኢንጂነር ወንድሙ፤ ብሎክ 13 ህንጻ ላይ የሚገኙ 29 አባወራዎች እና 150 ነዋሪዎችን ከስፍራው እንዲወጡ በማድረግ ቤቶቹ እንዲታሸጉ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተሽከርካሪም ሆነ በሰዎች እንቅስቃሴ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል ቦታውን ለእንቅስቃሴ ዝግ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ኢንጂነር ወንድሙ ተናግረዋል፡፡

ጉዳቱ እየተባባሰ እንዳይሄድም በአካባቢው ላይ ተጨማሪ ውኃ እንዳይኖርና የመሰጠንቅ አደጋዎች እንዳይከሰቱ በቀጣይ የማቅለያ እርምጃ የሚወሰድ ስለመሆኑም ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

በሜሮን ንብረት

#ebc #ebcdotstream #AddisAbaba #landslide