በአፋር ክልል በ2018 የትምህርት ዘመን ከ372 ሺህ በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንደሚገቡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
ከነዚህም መካከል ከ85 በመቶ በላይ ተማሪዎች በክልሉ ባሉ 1 ሺህ 204 ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መመዝገባቸውን የቢሮው ሀላፊ ሙሣ አደም (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የቀሪ ተማሪዎች ምዝገባ በቀጣይ አንድ ሳምንት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በትምህርት ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አክለዋል።
በክልሉ ከ600 በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት እንደሚሰጥ ቢሮ ሀላፊው ገልጸዋል።
ክልሉ ለፕሮግራሙ በሰጠው ትኩረት ለመስኖ ልማት ምቹ በሆነ አካባቢ የሚገኝ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት 3 ሄክታር መሬት አልምቶ በዘር እንዲሸፍን እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።
በትምህርት ለትውልድ መርሐ-ግብርም ለትምህርት ቤቶች ዕድሳት ከህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ እና በጉልበት በአጠቃላይ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገልጿል።
በክልሉ የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና ተፈታኞች የማለፍ ምጣኔን በ2016 የትምህርት ዘመን ከነበረበት 0.3 በመቶ በ2017 ወደ 1.3 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉም ተነስቷል።
በሁሴን መሐመድ
#EBCdotstream #Afar #Education