በትጋት ትምህርቴን በመከታተሌ እና በማጥናቴ ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ችያለሁ ሲል በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ 549 ያመጣው በሶማሊ ክልል፣ ጅግጅጋ ከተማ የ‘ዘ ስፓርክ’ አካዳሚ ተማሪው ሐምዛ ሻም መሐመድ ገለጸ።
ተጓዳኝ መጻሕፍትን በማንበብ፣ ያለፉ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን በመሥራት፤ ከባባድ ጥያቄዎች ሲያጋጥሙትም ከትምህርት ሰዓት ወጪ መምህራንን ጠይቆ በመረዳት ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ተማሪ ሐምዛ ይናገራል።
የራሱ ያላሰለሰ ጥረት፣ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር እና የመምህሮቹ ያልተቋረጠ እገዛ እንዲሁም የወላጆቹ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ ለውጤታማነቱ ትልቅ አስተዋፅዖ ማድረጉን በመግለጽ ምስጋና አቅርቧል።
የሕክምና ሙያ ተምሮ በጤና አገልግሎት ዘርፍ በመሰማራት ሀገሩን እና ህዝቡን ማገልገል የሐምዛ የወደፊት ዕቅዱ ነው።
አባቱ አቶ ሻም መሐመድ በበኩላቸው ልጃቸው ሐምዛ በአልባሌ ነገሮች ሳይዘናጋ ጠንክሮ በመሥራቱ ለውጤት መብቃቱን ገልጸው፤ በሂደቱ እርሳቸውም ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከማሟላት ጀምሮ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እገዛ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቢታንያ ሲሳይ
#Ethiopia #Education #12thgrade #Exam #highscore