Search

ኢትዮጵያ የፈፀመቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችባቸው ናቸው

ሓሙስ መስከረም 08, 2018 32

ኢትዮጵያ የፈፀመቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየችባቸው ናቸው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሃፅዮን  ገለጹ።

አቶ በረከት ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፈርጀ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች መፈፀም ችላለች ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት እንደ ሀገር የተከተልናቸው ስትራቴጂዎች ብዙ ልምድ ያስገኙ ናቸው ያሉት አቶ በረከት፤ በተለይም የፋይናንስ ሞዴላችን የተፈጥሮ ሀብትን ተጠቅሞ በራስ አቅም መልማት እንደሚቻል ያሳየንበት ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ ህብረተሰቡን እና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የተከናወኑ መሆናቸውን አንስተው፤ ይህ አሠራር በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎችም ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ተሞክሮዎቹ ህብረተሰቡን በልማት ሥራዎች በስፋት ማሳተፍ እና የሚያስፈልገውን ሀብትም በአግባቡ ማሰባሰብ እንደምንችል የታየባቸው እንደሆኑ ገልጸዋል።

አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶቹ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ያለፉ እንደነበሩ በማንሳትም ችግሮቹን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ሰፊ ልምድ የተገኘባቸው እንደሆኑ አውስተዋል።

ፕሮጀክቶቹ እንዳይፈፀሙ ከውጪም ከውስጥም ከፍተኛ ጫና ይደረግ እንደነበር አስታውሰው ይህን በፅናት በመቋቋም ፕሮጀክቶቹን መፈፀም መቻሉን አብራርተዋል።

በተለይ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኃይል አቅርቦቱም ቢሆን አምራች ኢንዱስትሪን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ በማድረግ ምጣኔ ሀብቷን በከፍተኛ ደረጃ ከመደገፍ ባሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርንም የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

በሐይማኖት ከበደ

#EBCdotstream #Ethiopia #MegaProjects #GERD