ዓለም በምዕራባውያን የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ብሪክስ የራሱን የፋይናንስ ተቋማት በመፍጠር ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ቡድኑ በተለይም አዲስ የልማት ባንክ (NDB) እና የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ስምምነት (CRA) የተባሉ ተቋማትን በመፍጠር ለኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እየጣረ ነው።
አዲስ የልማት ባንክ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ በተለየ መልኩ ከፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች ነፃ የሆነ የብድር አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
እስካሁን ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር የሰጠ ሲሆን፣ የአባል ሀገራትን የመሠረተ ልማት እና የዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶችን ይደግፋል።
አዳጊ ሀገራት ከምዕራባውያን ተቋማት ገንዘብ ለማግኘት በሚጣሉባቸው ፈታኝ ቅድመ ሁኔታዎች ምክንያት የብሪክስ የፋይናንስ ተቋማት አማራጭ የገንዘብ ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸው ተገልጿል።
በአሜሪካ ዶላር ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ እንዲቻልም ብሪክስ በአባል ሀገራት መካከል የገንዘብ ልውውጦችን ለማመቻቸት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
በተጨማሪም ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ ልውውጥን ለማሳለጥ ብሪክስ ፔይ የተሰኘ (BRICS PAY) የጋራ የክፍያ ሥርዓት ለመፍጠር ታቅዷል።
ብሪክስ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ሚዛናዊ ተቋም በመሆን የራሱን አሻራ እያሳረፈ ስለመሆኑም የአውስትራሊያ ኢንስቲቱዩት ኦፍ ፎረን አፌርስ መረጃ ጠቅሷል።
በሰለሞን ገዳ
#BRICS #Finance #NDB #CRA