አጀንዳ ለማባሰብ አቡዳቢ የሚገኘው የኮሚሽኑ ልዑክ ቡድን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከሚገኘው እና በዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ እና አካታች ውይይት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ከሚሰራው የአቡዳቢ የሰላም ፎረም ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን በምክክር በመፍታት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ልማት ለማዞር በመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገልፀዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ብዝሃነትን የማስተናገድ አቅም በመገንባታቸው ከራሳቸው አልፈው መላው የዓለምን ሕዝብ መሳብ እና ማዕከል መሆን መቻላቸውን አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያም ልዩነቶቿን በምክክር በመፍታት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ልማት ለማዞር በመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

የአቡዳቢ የሰላም ፎረም ዋና ፀሐፊ ከሊፋ አልዳህሪ (ዶ/ር)፤ የሰላም ፎረምን በመጠቀም ነባር የሰላም እሴቶችን በማጠናከር እና አሰባሳቢ ትርክት በማምጣት በቀጣናው የጽንፈኝነትን አስተሳሰብ ማዳከም ስለተቻለበት መንገድ ተሞክሮ አጋርተዋል።
ዋና ፀሐፊው የኢትዮጵያ የምክክር ሂደት የተሳካ እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት በመግለጽ፤ ፎረሙ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ሂደት እስኪጠናቀቅ ልምድ ለመለወጣጥና በሌሎች ቴክኒካዊ ትብብሮች ላይ በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ የሚያሰባስብበት የምክክር መድረክ ነገ ቅዳሜ መስከረም 10 ቀን 2018 በጁሜይራህ ክሪክሳይድ ሆቴል፣ በዱባይ ኤ አይ ጋርሁድ እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በላሉ ኢታላ