ከላይ የተጠቀሰውን ሀሳብ ያዘለ ጽሑፍ ዘ ዓረብ ዊኪሊ ላይ በዝርዝ ያሰፈረው በሱዳን እና በዓረብ ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ጸሐፊ እና ተንታኝ የሆነው ኤልፋዲል ኢብራሂም ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባለፉት አሥርት ዓመታት በዘመናዊው የውኃ ፖለቲካ ታሪክ ትልቁ የውኃ ጦርነት መንስኤ እንደሚሆን ብዙዎች ያምኑ እንደነበር ጸሐፊው ያነሳል።
ለዚህም እንደ ምክንያት ይጠቀስ የነበረው “ኢትዮጵያ የታችኛውን የተፋሰስ ሀገራት አደጋ ውስጥ የሚከት እና ታሪካዊ የውኃ ድርሻቸውን የሚቀንስ ግድብ እየገነባች መሆኑ” እንደሆነ አንስቷል፡፡
በዚህም መነሻነት ዓባይን እንደ ግሏ ንብረት ይዛ የቆየችው እና እንደ ደም ዝውውሯ የምትመለከተው ግብፅ ተገድዳ ወደ ግጭቱ ትገባለች የሚል ፍራቻ ነግሶ እንደነበር ያወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የተጠናቀቀውን ግድብ ሲመርቁ "በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ውስጥ ትልቁ ስኬት" በማለት የተናገሩለት ግድብ መጠናቀቅ ግን የነገሮችን አቅጣጭ እንደለወጠው ጠቅሷል ጸሐፊው።
ይህም ግብፅ በአንድ ወቅት እንደ ማስፈራሪያ እና ተፅዕኖ ማሳረፊያ ስትጠቀማቸው የነበሩት ያረጁ ውሎች እና "የውኃ ባለቤትነት ስምምነቶች" እንዳበቃላቸው አመላክቷል ብሏል።
በግብፅ ፊታውራሪነት ሲዘወር የነበረው የታችኛው ተፋሰስ ጥምረት ፈርሷል የሚለው ጸሐፊው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እነዚህ የተፋሰሱ ሀገራት ሌሎቹን ገለልተኛ ያደረጉበትን የተወሳሰበ ጨዋታ ቀይሮታል ይላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ካረጋገጣቸው የማይታጠፉ አዳዲስ እውነታዎች ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር የግብፅ ወታደራዊ አማራጭ በፍፁም መዘጋቱ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በአንድ ወቅት የጋዜጦችን እና የመገናኛ ብዙኃንን የፊት ገጾች ይቆጣጠር የነበሩት የጦርነት ፉከራዎች እና የይዋጣልን ጋጋታዎች አሁን ባዶ እንደሆኑም ኢብራሂም በጽሑፉ ውስጥ አጽንኦት ሰጥቶታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2020 “ግብፅ ያንን ግድብ ታፈነዳለች" የሚለውን ግልጽ ማስፈራሪያ የሚያስታውሰው ጸሐፊው፣ የፕሬዚዳንቱ መግለጫ የካይሮን ጽንፍ የረገጠ ፍላጎት ያንጸባረቀ ቢሆንም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ነበር ይላል።
ዛሬ ግድቡ እውን በመሆኑ ወታደራዊ አማራጭ የማይታሰብ እና የግብፅ እጆችም እንዲሰበሰቡ ያደረገ እንደሆነ ነው የሚጠቅሰው።
ይባስ ብሎም በጋዛ የተከሰተው አውዳሚ ጦርነት፣ እስራኤል በኳታር ላይ ያደረሰችው ጥቃት በካይሮ ላይ ሌላ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑ ደግሞ ፊቷን ወደ ሌላ እንድታዞር እንዳስገደዳት ያወሳል።
እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች እና የኢትዮጵያ ዝግጁነት ተደማምረው ግብፅ 125 ሚሊዮን ሕዝብ ካላት ኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ብትገባ የሚፈጠርባትን ቀውሰ እና አደጋ እንድትረዳ እንዳደረጋት ጸሐፊው ጠቅሷል።
ይህም ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ ብቻ ሳይሆን የፖሊሲ ጉዳይ ጭምር እንደሆነ የሚጠቅሰው ጸሐፊው፣ የግብፅ ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን እርምጃ "የህልውና ስጋት ነው" ማለታቸውን ቢቀጥሉም ፓሊሲ አውጪዎቻቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የሚያስተናግድ የፓሊሲ ማዕቀፍ እየነደፉ ነው ይላል።
ተጨባች ማስረጃውም ግብፅ ጨዋማውን የሜዴትራኒያን ውኃ በማጣራት ላይ እያደረገችው ያለው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እንደሆነ ማሳያ ያርባል።
የግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊ ሀገራቸው በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በየቀኑ አስር ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጨዋማ ውሃ ለማምረት ትልቅ እቅድ ማውጣቷን በቅርቡ አስታውቀዋል።
ግብፅ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ወደ 100 የሚጠጉ ጨዋማ ውኃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ማስገባቷ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ እና የውኃ ፓሊሲዋን ከነባራዊ እውነታ ጋር ለማስተካከል ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ይላል ጸሐፊው።
ይህ እንቅስቃሴዋ በአውሮፓውያኑ 1929 እና 1959 በቅኝ ግዛት ዘመን በተደረጉ ስምምነቶች የተደገፈው እና ለግብፅ የአንበሳውን ድርሻ የሰጠው የድሮው የሃይድሮ-ፖለቲካ ሥርዓት እንደማይሠራ መረዳቷን ማሳያ ነው ይላል ኢብራሂም።
እናም አሁን ካይሮ ግድቡን በማጥፋት ላይ ሳይሆን ግድቡን ማዕከል አድርጋ እያቀደች ነው በማለት ፖሊሲዋን ማስተካሏን ያወሳል።
"የግብፅ እጅ ታስሯል፤ በአንድ ወቅት ወሳኝ የግብፅ አጋር የነበረችው ሱዳን 2023 ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት ተይዛለች" የሚለው ጸሐፊው፣ ይህም ግብፅ በሕዳሴ ላይ የነበራትን የተዛባ አቋም ለማረም ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳል።
በ2019 በካርቱም የተፈረመው የመሪዎቹ የሦስትዮሽ ስምምነትም ሱዳን ቀድሞውንም ቢሆን የግድቡን አሞላል በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መሥራት የሚያዋጣት መሆኑን የተረዳችበት እንደሆነም ጸሐፊው ያትታል፡፡
ኢትዮጵያ ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች መሆኑን፣ በዚህም ሱዳን ያልከፈለችው 90 ሚሊዮን ዶላር የመብራት እዳ እንዳለባት ይጠቅስና ሱዳን በተግባር የምትሰለፈው በተጨባጭ ተጠቃሚ ካደረገቻት ኢትዮጵያ ጋር መሆኑን ያወሳል፡፡
ግብፅ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ጊዜያዊ ችግር ለመጠቀም ጥረት ብታደርግ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ባደረገችው ስምምነት ያኛውም በር እንደተዘጋበት ጠቅሷል ጸሐፊው።
የታችኛው ተፋሰስ ሀገሯ ደቡብ ሱዳን ደግሞ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዓባይ ልማት አርአያነት ለመከተል መወሰኗ እንደ ኬንያ ያሉ ሀገራትም ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛታቸው ሌላው ግብፅ የጦርነት ሀሳቧን እንድትገታ ያደረገ ጉዳይ እንደሆነ ያወሳል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ቁጭቶችን የተወጣችበት፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ፊታቸውን ቢያዞሩባትም በራሷ አቅም ግድቡን የገነባችበት፣ ግድቡን ለእውነተኛ ቀጣናዊ ውህደት ልትጠቀምበት የወሰነችበት መሆኑን በማጠቃለያው ያነሳል፡፡
እናም ኢትዮጵያውያን ግድቡን በመገንባት በዓባይ ታሪክ ውስጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጀምረዋል በማለት ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ምሥጢር እንደሆነ የጸፈው፡፡
ፕሮፌሰር እና የሕግ ጠበቃ የሆኑት ዓለማየሁ ገ/ማርያም የኤልፋዲል ኢብራሂምን ጽሑፍ "የታላቁ ኢትዮጵያ መጠናቀቅ ያለውን አንድምታ በጥልቀት የዳሰሰ በዕውት ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ነው" ብለውታል።
ትንታኔው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ‘ዓባይ ለግብፅ ጥቅም ብቻ የተፈጠረ ነው’ የሚለውን ያረጀ ትርክት የቀየረ መሆኑን በግልጽ ማሳየቱን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በኤክስ ገጻቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፍላጎት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ውህደት እና ብልጽግና መጠቀም እንደሆነም ፕሮፌሰር እግረ መንገዳቸውን ጠቅሰውታል።
በለሚ ታደሰ