Search

"በኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አታምኑም" - አሞስ ቶማስ(ዶ/ር)

ዓርብ መስከረም 09, 2018 196

"ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አታምኑም" ሲሉ ያደነቁት የናይጄሪያ ተወላጅ እና በአሁኑ ወቅት በሀገረ አሜሪካ ነዋሪ የሆኑት የአመራር እና የሥራ ፈጠራ አሰልጣኙ አሞስ ቶማስ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

 በቲክ ቶክ ገፃቸው የተለያዩ አፍሪካ ነክ ጉዳዮችን የሚዳስሱት ዶ/ር አሞስ፤ ኢትዮጵያ እያመጣችው ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ዳስሰዋል፡፡

 በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም ተስፋ እየሆነች ነው በማለት ነው የገለጹት፡፡

 "ስንቶቻችሁ በአዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ፈጣን ለውጥ አስተውላችኋል?" በማለት ይጠይቁና፣ "ኢትዮጵያ ምዕራቡ ዓለም እና መላው ዓለም እንኳን እየተደመመባቸው ያሉ ሥራዎችን እየሠራች ነው" ይላሉ፡፡

 "ማንም አሁን ኢትዮጵያ እያደገች እና እየተለወጠችበት ያለበትን ፍጥነት አያምንም" የሚሉት / አሞስ፤ የኢትዮጵያ ዕድገት ተአምራዊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

 "እኛ አሜሪካ እንዴት የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዳመጣች፣ ቻይናም እንዴት በኢንዱስትሪ እንደበለፀገች እናወራለን" ብለው፣ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ዕለት የኢንዱስትሪ አብዮት ማወጇን ጠቅሰዋል፡፡

 "አሁን ወደ አዲስ አበባ ስትሄዱ ሌላ የምዕራባውያን ከተማ ውስጥ እንዳላችሁ ሊሰማችሁ ይችላል" ሲሉ ነው የአዲስ አበባን ለውጥ የሚያወሱት፡፡

 "አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ሕንጻዎችን ውበት እና ግዝፈት ስትመለከቱ፣ በአንዱ የአሜሪካ ከተማ ውስጥ እንዳላችሁ ሊሰማችሁ ይችላል፤ ነገር ግን ያላችሁት አፍሪካ ውስጥ ነው! ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ" በማለት ነው ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህን ለውጥ ለማምጣት ራዕይ ያለው አመራር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ረገድ የታደለች ነች ብለዋል፡፡

ዕድገት አንዳንዴ ሕመም እንዳለው የጠቆሙት ዶ/ር አሞስ፣ ተግዳሮቱን ተቋቁሞ ወደ ፊት የሚወስድ አመራር ካለ ውጤቱ አስደሳች እንደሚሆን ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን በጀመረችው ፍጥነት ከቀጠለች በሚቀጥሉት አምስት እና አሥርት ዓመታት ውስጥ ሌላ ተናፋቂ ሀገር እንደምትሆን ነው ምስክርነታቸውን የሰጡት፡፡

አሞስ ቶማስ(/) "Life Legacy Investment Group" የተባለ የግላቸውን ድርጅት እየመሩ ሲሆን፣ "7 Big Lessons Africa Must Learn from Israeli-Iran Conflict" የሚል መጽሐፍም ጽፈዋል፡፡

በለሚታደሰ