የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የደንበኞቹን እርካታ የበለጠ ከፍ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎችን ማድረጉን የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ ገልጸዋል፡፡
አቶ ቢቂላ መዝገቡ በአዲስ አበባ አራት ተጨማሪ ቅርንጫፎች እየተከፈቱ መሆኑን ጠቁመው፤ አዳዲሶቹ ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው ቅርንጫፍ እንደሚዘጋ ተናግረዋል፡፡
የተገልጋዮችን እንግልት ለመቀነስም ቅርንጫፎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ከዚህ ሥራ ጋር የተያያዘ ሥራ በሚሰሩ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚበጅለትም ነው ያመላከቱት፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የደንበኞቹን እርካታ የበለጠ ከፍ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎችን እየደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አገልግሎቱ ካደረጋቸው ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የሥራ ሰዓት ማሻሻያ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቢቂላ፤ ከመስከረም 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽት 4 ሰዓት የፓስፓርት አግልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
ሌላው ማሻሻያ ሕብረተሰቡን ሲያማርር የነበረውን ሲስተም ቀልጣፋ ማድረግ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዚህም www.ethiopianpassportservices.gov.et የሚለውን ነባር ሲስተም ከማሻሻል በተጨማሪ www.immigration.gov.et የሚባል ተጨማሪ የአገልግሎት ማግኛ ድረ-ገፅ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ማንኛውም ሰው በቀላሉ ወደ ሲስተሞቹ ገብቶ ኦንላይን ማሟላት ያለበትን መረጃ ማስገባት እንጂ የማንኛውንም አካል ድጋፍ እንደማያስፈልገው ጠቅሰዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጎተራ እና ጥቁር አንበሳ ቅርንጫፎችን ጨምሮ በሌሎች የክልል ከተሞች በሚገኙ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የበዓል ቀናትን ጨምሮ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽት 4 ሰዓት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ተገልጋዮች እሁድ ከማለዳው 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉም ነው የተናገሩት።
ሲስተሙን እና የአገልግሎት ሰዓትን ከማሻሻል ጎን ለጎን፣ አገልግሎት የሚሰጠውን የሰው ኃይልም በእጥፍ የተጨመረ መሆኑን አቶ መዝገቡ ጠቁመዋል፡፡
ከነባር እና አዲስ ከሚከፈቱ ቅርንጫፎች በተጨማሪ በሁሉም የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሠራሩን ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከማድረግ አንጻር ሁሉንም አሠራሮች ከወረቀት ወደ ዲጂታል መቀየራቸውን ተናግረዋል።
ተቋሙ የረጅም ጊዜ ብልሽት የነበረበት መሆኑን ያነሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ችግሩን ለማቃለል ከውስጥ ሆነው ከደላላ ጋር ተመሳጥረው ተገልጋዩን ሲያማርሩ በነበሩት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ሠራተኞቹ ከተገልጋዮቹ ጋር የማይገናኙበት ሥርዓት እየተፈጠረ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት፡፡
በሕግ ተጠያቂ መደረግ ያለባቸውን ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ የነበረውን ብልሹ መረብ በጣጥሶ በአዲስ የሰው ኃይል የመተካት ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡
የነበረው ችግር እየተፈታ መሆኑን ተገልጋዩ በተግባር ማረጋገጥ እንደሚችል ገልጸው፤ ችግሮች ካሉም ለሚመለከተው አካል ብቻ ማስታወቅ እና እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
እየተወሰዱ ባሉ ማሻሻያዎችም ተገልጋዮች ኦንላይን ተመዝግበው፤ ፓስፖርታቸው እጃቸው እስከሚገባ ድረስ ከ3 እስከ 6 ወራት ድረስ ተራዝሞ የነበረው የቀጠሮ ጊዜ ወደ 2 ወራት ዝቅ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ የደንበኞቹን እርካታ ከፍ ለማድረግ ይህን ማሻሻያ እያደረገ ነገር ግን "ጉዳይ አስፈጽማለሁ" የሚል ደላላ ጋር የሚሄዱ ተገልጋዮች ራሳቸው ተጠያቂ እንደሚደረጉ አቶ ቢቂላ አስገንዝበዋል፡፡
መገናኛ ብዙኀን በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም የአገልግሎቱ ቅርንጫፎቹ ተገኝተው ተቋሙ ያሻሻላቸው የሰዓት፣ የሰው ኃይል እና የአገልግሎት አሰጣጥ ለውጦችን መመልከት እንደሚችሉም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #immigration #ethiopianimmigration #passport