ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያን ሀቅ አንሻፈው እና አጣመው ለሚናገሩ አካላት በመከታተል ትክክለኛውን እውነታ ለዓለም አስረድተናል ሲሉ የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ፡፡
ኡስታዝ ጀማል ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጠላቶች በተሳሳቱ የቀድሞ ውሎች ምክንያት ኢትዮጵያ እንደቀኝ ግዛት ሁሉ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ለማድረግ የሄዱበት ርቀት ኢ-ፍትሀዊ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የተሳሳተ ሀሳባቸውን በማረም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መሟገታቸውንም ኡስታዝ ጀማል ገልጸዋል፡፡
ይህም ብዙዎች የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እና ኢትዮጵያዊያን ሀቅ አላቸው ብለው እንዲገነዘቡ እንዳስቻለም አንስተዋል፡፡
እንደ አፍሪካ የተነዛው የተሳሳተ ትርክት ልክ ባይሆንም ኢትዮጵያ ብቻዋን ያለማንም አጋዥ እና ደጋፊ ትርክቱን በጣጥሳ አልፋ ግዙፉን ግድብ መገንባት ችላለች ብለዋል፡፡
አሁን ላይ አፍሪካዊያን አደረግነው አሳካነው እያሉ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ግድቡ ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ኩራት እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የግድቡ ስኬት ከኛ አልፎ ጠላቶች ስለ እኛ እየመሰከሩ ነው ያሉት ኡስታዝ ጀማል፤ አይችሉም አይሳካላቸውም የሚለው መንፈስ ተቀይሮ ሰሩት የሚሉ ሀሳቦች እየተንፀባረቁ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡን በትውልድ ቅብብሎሽ እውን ማድረግ መቻሉንም ነው የጠቀሱት፡፡
ይህም በተለያየ አስተሳሰብ ያሉ ግን በሀገር ጉዳይ አንድ የሆኑ ዜጎች ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን ማሳካት እንደሚችሉ ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡
በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ ሳንከፋፈል ህዳሴን እውን ማድረግ ችለናል ያሉት ኡስታዝ ጀማል፤ በሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ድሉን መድገም እንደምንችል ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD