የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ “በህብረት ችለናል” በሚል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝባዊ የድጋፋ ሰልፍ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሕዳሴ ግድብ ለዘመናት የኢትዮጵያውያን ቁጭት ሆኖ የቆየውን የአገር ሀብት ወደ ጥቅም የቀየረ፤ የመንግሥትን ጥበብ የተሞላበት አመራር ያሳየ ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁ አንድ ስንሆን፣ ስንተባበር የማንችለው ነገር እንደማይኖር እና እንደ ሀገር የወል ትርክት ላይ ልንሠራ እንደሚገባ ያሳየ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ማሳያ ነው ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የሆሳዕና ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ “በህብረት ችለናል፤ ችለን አሳይተናል፤ ግድቡ የእኔ፣ የአንተ፣ የአንቺ እና የሁላችንም ነው፤ አንድ ስንሆን እንበረታለን” የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶችን አስተጋብተዋል።
ሕዳሴ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ማሳያ ነው ያሉት ሰልፈኞቹ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጉባ ብስራት ይፋ በተደረጉ ትላልቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችም በንቃት ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሀድያ ዞን፣ ሆሳህና ከተማ በተደረገው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮችም ተገኝተዋል።
በሰናይት ብርሀኔ
#EBCdotstream #Ethiopia #GERD #ሕዳሴግድብ