ዮዮ ጊፋታ!
ዮ ማስቃላ!
ዮ ጋዜ ማስቃላ!
ዮኦ ማስቃላ!
ዮዮ ባላ ካዳቤ!
ዮዮ ቡዶ ኬሶ!
እንኳን ለወላይታ፤ ለጋሞ እና ለጎፋ ዞን ሕዝቦች የብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓላት በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
ብዝኃነት እና ህብረ-ብሄራዊነት መለያው የሆነው የሰላም ተምሳሌቱ ክልላችን፤ የበርካታ ውብ ባህሎች እና የኅብር ማንነቶች ባለቤት የሆኑ የየራሳቸው የጊዜ ቀመርና የዘመን መለወጫ በዓላት ያሏቸው ሕዝቦች የጋራ ቤት ነው፡፡
በወርሃ መስከረም መባቻ በዘመናት አብሮነት የተዛመዱ፤ የተጋመዱ እና ባህል እሴቶቻቸውን ተወራርሰው የተሠናሠሉት የወላይታ፤ የጋሞ እና የጎፋ ዞን ህዝቦች በየራሳቸው የጊዜ ቀመር የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ፤ የብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸውን በአዲስ መንፈስ፤ በብሩህ ተስፋ ተሞልተው በታላቅ ድምቀት ያከብራሉ፡፡
በዓላቱ እንደየብሄረሰቡ ትውፊትና ባህላዊ ዕሴት፡- በወላይታ 'ዮዮ ጊፋታ'፣ በጋሞ 'ዮ ማስቃላ'፣ በጎፋዎች ዘንድ 'ጋዜ ማስቃላ'፤ በኦይዳ ብሄረሰብ 'ዮኦ ማስቃላ' በዛይሴ 'ቡዶ ኬሶ' እንዲሁም በጊዲቾ 'ባላ ካዳቤ' በሚል በተቀራረበ ወቅት ከዘመን ዘመን ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ ጭምር በአብሮነት የሚከበሩ ድንቅ እሴቶቻችን ናቸው፡፡
የክረምቱ ጭጋግና ጨለማ ተገፍፎ ብርሃን በሚፈነጥቅበት፤ እርሻው በመኽር አዝመራ አረንጓዴ ለብሶ ብሩህ ተስፋን በሚሰንቅበት ወቅት የሚከበሩት በዓላቱ፤ ፈተና የበዛበት የዝናብ ወቅት ማለፉን በማብሰር አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት በብሩህ ተስፋ የሚቀበሉበት፣ የተራራቁና የተነፋፈቁ የሚገናኙበት እና የተጣሉ የሚታረቁበትም ነው፡፡
በዓላቱ የህዝቦቻችንን ዘመናት የተሻገረ አብሮነት፤ የርስ በርስ መስተጋብር እና ትስስር በሚያንፀባርቁ ተቀራራቢ ይዘት ባላቸው የተለያዩ ስርዓቶች፤ በተለይም የእርቅ፤ የሰላም፤ የአንድነት፤ የመደጋገፍና የወንድማማችነት እሴቶችን ባቀፉ ባህላዊ ሁነቶች የሚከበሩ በመሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በሁሉም አካባቢዎች በዓላቱ ሲከበሩ የተቃቃሩና የተጣሉ ታርቀው፤ ፀብና ቁርሾም በይቅርታ ተሽሮ፤ የጥላቻ ግንብ ፈርሶ፥ ሰላምና ፍቅር ይነግሳል፤ አብሮነትና አንድነት ይበልጥ ይጐለብታል፤ መተሳሰብና መረዳዳትም ያብባል፡፡
በዓላቱ ዘንድሮ በተለየ በመላ ኢትዮጵያዊያን የተደመረ አቅምና የዓላማ ጽናት ታላቁ የሕዳሴ ግድባችንን በድል ባጠናቀቅንበት እና የኢትዮጵያን የማንሠራራት ምዕራፍ ጅማሮ ባበሰርንበት ወቅት የሚከበሩ እንደመሆኑ፤ ከአዲስ ዓመት የብሩህ ተስፋ ስንቅ ጋር ትብብራችንን አጠናክረን ለሌላ ታላቅ ስኬት የምንዘጋጅበት ሊሆኑ ይገባል፡፡

ብዝኃነት ጌጣችን በሆነው ክልላችን፥ በዓላቱ ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን በብዝኃነት ውስጥ ያበቡ የአንድነት ግማዶቻችን እጅግ የበዙ መሆኑን በጉልህ የሚያንፀባርቁ ዓውዳቻችንም ናቸው፡፡
በመሆኑም በዓላቱን ስናከብር በጥቃቅን ልዩነቶች የኋላት ከመሳሳብ ይልቅ ከጽኑ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችን የሚመነጩ የኅብረት፤ የመተባባርና የመደጋገፍ እሴቶቻችንን በማጎልበት ለጋራ ሰላም፤ ልማትና ሁለንተናዊ ብልጽግና በጋር ለመትጋት በመነሳት መሆን ይኖርበታል፡፡
አባቶች ጠብቀው ያቆዩልንን እኚህን ድንቅ የሰላምና የአንድነት እሴቶች ያቀፉ በዓላት ከነሙሉ ባህላዊ ይዘታቸውና ስርዓታቸው ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ከማሻገር ባላፈ የበዓላቱን አከባበር በማስተዋወቅ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ መስራት ይገባል፡፡
አዲሱ ዘመን ሰላም፤ ፍቅርና አንድነት የሚያብብበት፤ ኅብረትና ትብብራችን ከፍ ብሎ ለታላቅ ስኬት የሚንበቃበት እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ።

መልካም በዓል!
ዮ ዮ ዮ ዮ ዮ ..........