በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው “የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት” በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችና የከተማ አስተዳደሮች ልምድ ተወስዶበተስ የተፈረመው የፋሲለደስ ዴክላሬሽን ሀገር አቀፍ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ማብሰሪያ መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።
“ማኅበራዊ ትስስራችን፣ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን የማብሰሪያ መርሐ-ግብር ያስጀመሩት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት የማኅበራዊ ትስስርና የአብሮነት ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“የጎንደር ቤተሰብ ፕሮጀክት” በሚል ስያሜ በ2012 ዓ.ም የተጀመረው ይህ ፕሮግራም፤ በየዓመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ዩኒቨርስቲው የሚመደቡ ተማሪዎችን በመቀበል፤ ከጎንደር ከተማ ማኅበረሰብና ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የቃል ኪዳን ቤተሰብ በመምረጥና በማስተዋቅ የማስተሳሰር ዓላማን ያነገበ መርሐ-ግብር መሆኑን አንስተዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው ፕሮግራም ተቋማዊ አሠራርን እንዲከተል በማድረግ ሀገር አቀፍ መልክ እንዲኖረው የሚያስችል ሥራ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት እየተከናወነ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በሀገር አቀፍ የቃል ኪዳን ቤተሰብ ማብሰሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የከተማ አስተዳደር ተወካዮች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች እና ሀደ ሲንቄዎች ታድመዋል።
በዮሐንስ ፈንታሁን
#Ethiopia #UniversityofGondar #GondarFamilyProject #MinistryofPeace