Search

የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተሳካ ሁኔታ እንዲከበሩ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል

ቅዳሜ መስከረም 10, 2018 204

የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተሳካ ሁኔታ እንዲከበሩ ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ገለፁ።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል፤ ዘንድሮ ከአዲስ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ የኢትዮጵያን ከፍታ ያሳዩ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች እየተስተናገዱ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ለአብነትም ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ የአፍሪካ የካረቢያን ጉባኤ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ፣ ምረቃውን አስመልክቶ የተካሄዱ እና እየተካሄዱ የሚገኙ የደስታ መግለጫ ሰልፎች ያለምንም ስጋት በስኬት መቀጠላቸውን አንስተዋል።
ለዚህም የፖሊስና የሌሎች የፀጥታ ተቋማት ሚና የላቀ መሆኑን አመላክተዋል።
በመስከረም ወር ሕዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ከሚያከብራቸው በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት በተከታታይ እንደሚከበሩ ገልጸው፤ ለዚህም ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢ በድምቀት የሚከበር የአደባባይ በዓል መሆኑን ጠቁመው፥ በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ፖሊስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዝግጅት ማድርጉን ገልጸዋል።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመታደም የሚገኙ ቱሪስቶች ሰላምና ደህንነታቸው ተጠብቆ የቆይታ ጊዜያቸው ያማረ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በርካታ ሕዝብ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ የሚታደምበት የኢሬቻ በዓል በተሳካ መልኩ እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ለሚደረጉ ታላላቅ ሀገራዊና ሕዝባዊ ሁነቶች እና በዓላት በድምቀት መካሄድ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።