ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራውን ያኖረበት የወል ትርክት ነው ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰመራ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም፤ ህዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች በሙሉ ዳግማዊ ዓድዋ እና የድል ምልክት ነው ብለዋል።
ግድቡ በትውልድ ቅብብሎሽ በህዝቡ ዘንድ የነበረው ቁጭት ወደ ድል እና ብልፅግና የተቀየረበት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የአፋር ህዝብ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከመጠበቅ በላይ የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ በሀብት፣ በሀሳብና በፃሎትም ጭምር አብሮነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ለግድቡ ከውጭ የሚገቡ ንብረቶች በሰላም እና በጥንቃቄ እንዲገቡ በማሳለፍ ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በህዳሴው ግድብ ያሳየውን ህብረትና አንድነት በማጠናከር በዲፕሎማሲያው መንገድ የባህር በር ባለቤትነቱን እንደሚያስመልስ ምንም ጥርጥር የለውም ሲሉም ተናግረዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በቀጣይ የውስጥ ሰላማችንን በማጠናከር በህዳሴ ግድብ ላይ የታየውን ርብርብ በሌሎች ልማቶችም ላይ መድገም ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል።
በሁሴን መሀመድ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD #Afar