ኢትዮጵያውያን ተደምረው የሕዳሴ ግድብን የገነቡበት መንገድ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን የሚያነቃቃ መሆኑን ‘ዲጄ ፋብ’ በሚል የቲክ ቶክ ስሙ የሚታወቀው ቲክቶከር ተናግሯል።
"ኢትዮጵያ ዳግም ታሪክ ሠራች፤ ከብዙ ፈተናዎች በኋላ የሕዳሴ ግድብን አጠናቀቀች፤ ይህም ከአፍሪካ ለአፍሪካውያን የተሠራ ትልቅ ፕሮጀከት ነው" ብሏል።
ኢትዮጵያውያን ያለምንም ብድር እና ዕርዳታ በራሳቸው ወጪ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት አስጋራሚ ታሪክ ሠርተዋል ሲልም አክሏል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ተጠናቅቆ መመረቁ ለአፍሪካ ትልቅ ዜና መሆኑን እና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አፍሪካውያን የሚጠቅም እንደሆነ በመልዕክቱ አመላክቷል።
በአፍሪካ በቅኝ ግዛት ያልተያዘችው ብቸኛ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ ከተባበሩ እጅግ ጠንካራ ሕዝቦች መሆናቸውን በሕዳሴ ግድብ ዳግም በተግባር ማሳየት መቻሏን አንሥቷል።
በቅኝ ግዛት ሊይዟት የመጡትን ወራሪ ኃይሎች በአይበገሬ ልጆቿ መክታ ወደ መጡበት መመለሷንም ጠቅሷል።
ኢትዮጵያውያን በሕዳሴ ግድብ ዳግማዊ ዓድዋን በተግባር ማሳየት በመቻላቸው ለአፍሪካውያን የይቻለል መንፈስን በማስታጠቅ ትልቅ መነሣሣት የፈጠረ መሆኑን ተናግሯል።
አፍሪካውን ሀብታቸውን በራሳቸው አቅም ከልብ ማልማት ከቻሉ በዓለም ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝብ እና ሕዝባቸውን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚችሉ ኢትዮጵያ ምርጥ ማሳያ ናት ብሏል ዲጄ ፋብ በመልዕክቱ።
በላሉ ኢታላ
#GERD #Ethiopia #Africa #victory