Search

በወላይታ ብሔር ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው "ጊፋታ”

እሑድ መስከረም 11, 2018 67

"ጊፋታ” የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ነው።

የወላይታ ብሔር የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች አሉት።

የአለባበስ፣ የበዓላት አከባበር፣ የለቅሶ እንዲሁም የጋብቻ ሥርዓተ ክዋኔዎች እና ሌሎችም የወላይታ ብሔር በራሱ ባህላዊ ይዘት የሚከውናቸው እሴቶች ናቸው።

የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነው "ጊፋታ" በዓልም በብሔሩ ዘንድ የተለየ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው።  

የወላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ ቀመር አለው። በዚህ በአቆጣጠር መሰረትም የዓመቱ የመጀመሪያ ወር "ጊፋታ" ይባላል። የቃሉ ትርጓሜ ‘ባይራ (ታላቅ)፣ የመጀመሪያ፣ በኩር’ ማለት ነው።

በዓሉ ከመስከረም 8 እስከ 14 ባለው አንዱ እሁድ በጉጉት እና በከፍተኛ ዝግጅት በየዓመቱ የሚከበር የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል ነው።

"ጊፋታ" በብሔሩ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እና ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የአሮጌ ዓመት ማብቂያ እና የአዲሱ ዓመት ማብሰሪያ ነው።  

"ጊፋታ" ከአሮጌ ወደ አዲስ ተስፋ፣ ከክረምት ወደ በጋ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት የሚሸጋገሩበት ነው።

በብሔሩ ዘንድ የ"ጊፋታ" በዓል የዕርቅ በዓል እንደሆነም ይታመናል። ስለሆነም የ"ጊፋታ" በዓል ሲቃረብ የተጣላ ዘመድ፣ ጎረቤት፣ ቤተሰብ እንዲሁም ጓደኛ ይታረቃሉ። 

ማንም ሰው የ"ጊፋታ"ን በዓል ባለዕዳ ሆኖ ማክበር አይችልም። ስለሆነም የጊፋታ በዓል ሲደርስ ሰው ከዕዳ ነፃ መሆን ይጠበቅበታል። ይህም ይታወቃልና ሁሉም ሰው ከበዓሉ ቀድሞ ዕዳውን ከፍሎ በዓሉን ለማክበር ይዘጋጃል።

የጊፋታ በዓል እየተቃረበ መምጣቱን የሚገልጹ የተለያዩ ክዋኔዎች አሉ፤ ከክዋኔዎቹም መካከልም በወጣቶች ለጉሊያ (ደመራ) የሚሆን እንጨት መሰብሰብ እና መከመር እንዲሁም በእናቶች የሚከናወን የእንሰት መፋቅ ሥነ ሥርዓቶች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ክዋኔዎች የበዓሉ መዳረሻ ማብሰሪያ ምልክቶች ናቸው። 

አባቶች ዓመት ሙሉ በየወሩ የቆጠቡትን ገንዘብ ሰብስበው ገበያ ሄደው ሙክት እና በሬ የሚገዙበት ሥርዓትም ለበዓሉ የራሱን ድምቀት የሚሰጠው እንቅስቃሴ ነው። የእርድ በሬ ከሶስት ወር ቀደም ተብሎ ተገዝቶ እስከ ዕርዱ ቀን በአንድ አባወራ ቤት እንዲቀለብ ይደረጋል። 

ለበዓሉ መዳረሻ አስራ አምስት ቀን ቀደም ብሎ ሶስት ከወትሮው በተለየ ግብይት የሚከናወንባቸው ገበያዎች አሉ። እነዚህም "ሀራይቆ፣ ቦቦደ እና ጎሻ" ይባላሉ። የሀራይቆ ገበያ ማኅበረሰቡ የጊፋታ በዓልን ታሳቢ አድርጎ ምርት በገፍ የሚያቀርብበት እና የጋማ ከብቶችም ወገባቸው እስኪጎብጥ ድረስ ስለሚሸከሙ፣ “የጋማ ከብት የሚያጎብጥ” ገበያ ተብሎ ይታወቃል።  

ሌላኛው "ቦቦዳ" ገበያ ሲሆን ገበያው ጥሩ መዓዛ ያለው ገበያ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ገበያ ሁሉም ሰው በአቅሙ የሚያስፈልገውን የሚገዛበት ነው።

በ"ጎሻ" ገበያ ደግሞ ሁሉም ገበያተኛ ቁርስ ሳይበላ በማለዳ የሚያቀናበት ነው። "ጎሻ" የቃሉ ትርጉም እብደት ማለት ሲሆን፣ የመጨረሻው ሣምንት ገበያ በመሆኑ ሁሉንም ነገር የሚገዙበት እና በጧት ተነስተው ወደ ገበያ የሚያቀኑቡት በመሆኑ ጎሻ ተብሎ ይጠራል።  

ቁጠባ የጊፋታ ሌላኛው መገለጫ ሲሆን፣ በዓሉ በሚከበርበት ቀን ዕርድ ከተከናወነ በኋላ በእርጥብ ቆዳ ላይ ተቀማጭ ብር በማዋጣት ለመጪው ዓመት ጊፋታ ቁጠባ ይጀምራል። በቁጠባው ሴቶች በምግብ ቅቤ ቁጠባ፣ ወጣቶች በገንዘብ ቁጠባ ይሳተፉበታል ።

በብሔሩ ዘመን አቆጣጠር ቀመር መሠረት የዘንድሮ የጊፋታ በዓል መስከረም 11 ቀን 2018 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ "ጊፋታ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በድምቀት እየተከበረ ነው። 

YOO YOO GIFAATAA

በትግስቱ ቡቼ

#EBC #ebcdotstream #Wolaita #Gifata #yoyogifata