የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፈልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ "ጠላቶቿ ለውስጥ ባንዳዎች ገንዘብ በመክፈል እና በማደራጀት ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር በመመከት ሀገራችሁን ማሻገር አለባችሁ" ሲሉ በሁርሶ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ለተመረቁ ዕጩ መኮንኖች ተናገሩ፡፡
የሁርሶ እጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን የ26 ኛ ዙር ንሥር ኮርስ እጩ መኮንኖችን አስመርቋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ በጥቂት የውስጥ ባንዳዎች ስትፈተን ነበር፤ በአርበኛ ልጆቿ ግን ድል ስታደርግ ቆይታለች ብለዋል፡፡
"በዘመናችንም ታሪካዊ ጠላቶቻችን የውስጥ ባንዳዎችን በገንዘብ በመደገፍ ሀገር እንዳታድግ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በጀግና ሠራዊታችን እና በአርበኛ ሕዝባችን ድል እናደርጋለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሁርሶ እጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫጮ በበኩላቸው፤ ትምህርት እና ሥልጠናው ጠላቶቻችን ታሳቢ ያደረገ መደበኛ እና ኢ-መደበኛ የውጊያ ስልቶች ላይ ትኩረት በመስጠት በማንኛውም ሁኔታ እና ጊዜ ድል ማድረግ የሚያስችል አቅም የተፈጠረበት ነው ብለዋል፡፡
ተመራቂ እጩ መኮኝኖች በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የሚቃጣባትን የትኛውም ዓይነት ጥቃት ለመመከት እና የአፀፋ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአካል ብቃት በተኩስ፣ በወታደራዊ አመራርና ስልት በማዕከሉ ሥልጠና ሲሰጣቸው የነበሩ እጩ መኮንኖች በሥልጠናው ተጨማሪ አቅም የተፈጠረላቸው እና ተልዕኮዎችን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ የሚያደርገቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
በቶማስ ሀይሉ
#EBC #ebcdotstream #ENDF