የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ለወላይታ፣ ለጎፋ እና ጋሞ ዞን ሕዝቦች ዘመን መለወጫ በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስትሯ በእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው እንደገለጹት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበርካታ ውብ ባህሎች፣ እሴቶች፣ ታሪኮች እና የብዝኃ ማንነቶች ባለቤት የሆነ ክልል ነው።
ከዚህ ውስጥ የወላይታ፣ የጋሞ እና የጎፋ ዞን ሕዝቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በዓላቱ እንደየብሔረሰቡ ትውፊት እና ባህላዊ ዕሴት፡- በወላይታ ‘ዮዮ ጊፋታ'፣ በጋሞ ‘ዮ ማስቃላ'፣ በጎፋዎች ዘንድ ‘ጋዜ ማስቃላ'፤ በኦይዳ ብሔረሰብ ‘ዮኦ ማስቃላ' በሚል ስያሜ እንደሚከበሩም ገልጸዋል።
እንዲሁም በዛይሴ ‘ቡዶ ኬሶ' እና በጊዲቾ ‘ባላ ካዳቤ' በሚል በተቀራረበ ወቅት ከዘመን ዘመን ላሸጋገረ ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ፣ በአብሮነት እና በአንድነት የሚከበሩ ድንቅ እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።
የበዓላቱ አከባበር የሕዝቡን የሺህ ዘመናት አብሮነትን፣ የእርስ በርስ መስተጋብር እና ትሥሥር ከማንፀባረቃቸውም በላይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳላቸው ሚኒስትር ሸዊት ገልጸዋል።
ስለሆነም ይህንን ውብ ባህል በመጠበቅ እና በማልማት የበለጠ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የአብሮነት እና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
#Ethiopia #YooYooGifaataa #YooMaskala #YoGazeMaskala #YooOMaskala #YooYooBalaKadabe #YooYooBudoKeso