Search

በትግራይ 2 ነጥብ 57 ሚሊየን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ይደረጋል - የትግራይ ትምህርት ቢሮ

ሰኞ መስከረም 12, 2018 143

በትግራይ ክልል የ2018 የትምህርት ዘመን ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ፣ የመቐለ ከተማ ትምህርት ፅህፈት ቤት እና የክልሉ መምህራን ማኅበር ተወካዮች በመቐለ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ተገኝተው የትምህርት አጀማመሩን ተመልክተዋል።
የትግራይ ትምህርት ቢሮ በተያዘው የትምህርት ዘመን 2 ነጥብ 57 ሚሊየን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለማስገባት ማቀዱን አስታውቋል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢስማዒል አብዱራህማን ከነሐሴ 19 ቀን 2017 ጀምሮ የትምህርት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከነሐሴ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የተማሪዎች ምዝገባ መከናወኑን ገልፀዋል።
በከተሞች አካባቢ የተሻለ ሥራ ቢሰራም በተለይ በገጠር አካባቢ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይ በትምህርት አጀማመሩ ላይ ውስንነቶች ተስተውለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ወላጆች ልጆቻቸውን በፍጥነት ወደ ትምህርት ገበታ በመላክ ተማሪዎች የሚያልፋቸው የትምህርት ጊዜ እና ዕውቀት እንዳይኖር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በግጭት ምክንያት የባከኑት የትምህር ዘመናትን ለማካካስ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ኃላፊ አመላክተው፤ በዘንድሮ ዓመት የትምህርት ጥራቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
መምህራን እና ተማሪዎች በበኩላቸው የትምህርት ዘመኑ የተሳካ እንዲሆን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
 
በሙሉጌታ ተስፋይ