በምዕራብ ወለጋ ዞን የሕዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተሊላ ተረፈ እንደገለጹት፤ ቀደም ባለው ጊዜ በዞኑ የነበረው የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
በዚህ ወቅት በዞኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ 350 የሚደርሱ የመሰረተ ልማት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ነው ያሉት።
የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ተቋማትን ግንባታ በተያዘው በጀት ዓመት ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁም እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ትምህርት ቤቶች፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፣ የመንገድ እና የመብራት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚቀርፉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የግብርና ልማት ስራን የሚያሻሽሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
በተለይም በአካባቢው በስፋት እየለማ የሚገኘው የቡና ምርት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለገበያ በማቅረብ አምራቹንና ሀገርን ለመጥቀም ትኩረት መደረጉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌላ በኩል በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ማዕድናትን ለማውጣት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ የቱሪዝም መስህቦችን የማልማት ስራም ትኩረት ማግኘቱን ነው የተናገሩት።