በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ተማሪ ኃይማኖት ዮናስ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ 579 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበች ተማሪ ነች፡፡
በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ኃይማኖት፤ የብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን፤ የ2017 የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን በሴቶች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት አጠናቃለች።
ተማሪ ኃይማኖት በልጅነቷ ትምህርቷ ላይ ትኩረት አድርጋ የምትሰራ ቢሆንም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በምትማርበት ወቅት የደረጃ ተማሪ እንዳልነበረች ትናገራለች።
ታድያ ውጤቷን ለማሻሻል ለትምህርቷ የበለጠ ትኩረት ሰጥታ ማጥናት እንደጀመረች የምትገልፀው ተማሪ ኃይማኖት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የአንደኝነት ደረጃን የያዝኩት የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው ትላለች።
ከ 6ኛ ክፍል ጀምሮ የያዘችውን የአንደኝነት ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ይዛ መዝለቋን የምትገልፀው ኃይማኖት፤ ለትምህርት ቅድሚያ በመስጠት ትኩረት ሰጥቶ ማንበብ ከተቻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ትናገራለች።
በትምህርት ቤት ቆይታዋ ከመምህራኖቿ እና ከጓደኞቿ ጋር መልካም ጊዜ እንደነበራትና ይህም ለውጤት እንዳበቃት ትጠቅሳለች።
እኔ እራሴን ከማምነው በላይ እርግጠኛ ሆነው የሚተማመኑብኝ መምህራኖቼ እና ቤተሰቦቼ ነበሩ ለዚህ እንድበቃም ትልቅ ድጋፍ ሲያደርጉልኝ ነበር ስትልም ትናገራለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ስትከታተል አራቱንም ዓመት በትኩረት ስትሰራ የነበረ ሲሆን፤ በተለየ መልኩ የ12ኛ ክፍል ትምህርቷን ለፈተና በመዘጋጀት ጊዜዋን ታሳልፍ እንደነበር ገልፃለች።
ተማሪ ኃይማኖት ለፈተናው የሚረዷትን መፅሀፍት እና ጥያቄዎች በአግባቡ ትኩረት ሰጥታ ታጠና እንደነበር አንስታ፤ ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ያላት የተገደበ መስተጋብር ይበልጥ ለውጤት እንዳበቃት ትናገራለች።
ማንኛውም ሰው በተለይም ተማሪዎች ቴክኖሎጂን ለተሰማሩበትና ለፈለጉት ዓለማ መጠቀም እንጂ፤ ሚጠቅመውንም ማይጠቅመውንም እያዩ ጊዜያቸውን በከንቱ ማጥፋት እንደሌለባቸው ትመክራለች።
ተማሪ ኃይማኖት ኒዩሮ ሳይንስ የመማር ፍላጎት ያላት ሲሆን ወደፊትም በዚሁ ዘርፍ ለሀገሯ የሚጠቅም ስራ የመስራት ህልም እንዳላት ገልፃለች።
በሔለን ተስፋዬ
#ebc #ebcdotstream #Education #12thgrade #highscore