የመደመር መንግሥት መጽሐፍ መነሻ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መሆኑን "የመደመር ወግ" በሚል ርዕስ መጽሐፉን በተመለከተ በኢቲቪ ስቱዲዮ ውይይት ያደረጉት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
መደመር በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግሥት አወቃቀር ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ ኢትዮጵያ የመጣችበትን እና በዚያ ሂደት ምን ምን ጥንካሬዎች እና ክፍተቶች እንደነበሩ በማሳየት እንደሚጀምር የገለጹት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው።
መፅሐፉ የእነዚያን አመጣጥ ሲመለከት ግን ድክመቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን ጥንካሬዎቻቸውን ጠቅሶ ከዚያ የሚወሰዱ ወረቶችን እንደሚጠቁምም ነው የጠቀሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መደመር ላይ የጻፏቸው አራቱም መጽሐፍት ተያያዥ እና እርስ በርሳቸው የሚናበቡ እንደሆኑ ተናግረዋል።
መጽሐፍቱ ላይ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ ሁሉም ትውልድ የራሱን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉ በመደመር ትውልድ ላይ መጠቀሱን አውስተው፣ ስብራቶችን ማስተካከል የሚችለው ትውልድ ደግሞ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት በግልጽ ማመላከቱን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አራተኛው መጽሐፍ፣ “የመደመር መንግሥት”፣ በተከታታይ የመጣው የመደመር ፍልስፍና አካል እንደሆነ እና ፍልስፍናውን መሬት የሚያወርደው መንግሥት ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት በግልጽ ያስቀመጠ እንደሆነም ዶክተር ፍጹም አብራርተዋል።
የፍልስፍና ምሁሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) የሚኒስትሯን ሐሳብ ይጋራሉ። እርሳቸው እንዳሉት አራቱም መጽሐፍት በደንብ የሚናበብ ግንኙነት አላቸው።
ታሪካዊ ዳራ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትልቅ ቦታ እንዳለው የሚጠቅሱት ዶክተር ዳኛቸው፣ ታሪክን የሚጠቅሱት ግን ዝም ብሎ ለክርክር እና ሙግት ሳይሆን ድባብ ለመፍጠር እና ነባራዊ ሁኔታን ለመለየት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በመፅሀፉ ዙሪያ በኢቲቪ ስቱዲዮ ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ የመደመር ፅንሰ ሀሳብ የመጨመር ለውጥ ፍልስፍና ላይ በዋናነት ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የመጨመር ፍልስፍና ውስጥ ቀጣይነት እና ለውጥ እንዳለ የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፣ የመደመር መንግሥት መፅሀፍ ታሪክን በአውዱ በመረዳት የመጨመር ፍልስፍና ወይም መደመር በየወቅቶቹ ባለመኖራቸው ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖራት ማድረጉን እንደሚያትት ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #መደመር #YemedemerMengist