የመደመር ፅንሰ ሀሳብ የመጨመር ለውጥ ፍልስፍና መሆኑን በመደመር ወግ በኢቲቪ ስቱዲዮ ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ ተናግረዋል።
የመጨመር ለውጥ ውስጥ ቀጣይነት እና የሁኔታዎች መለዋወጥ እንዳለ የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፣ ይህንን በታሪክ አረዳድ ከተመለከትነው ያልተዘጋ መቼት አለው ብለዋል።
"መደመር መቼትን አስቀምጦ ባለፉት ነገሮች ላይም ብይን ሲሰጥ እንኳን እዚያ ጫማ ውስጥ ገብቶ ነው" ያሉት አቶ ዘሪሁን፣ ጉዳዮቹንም ሲያስቀምጥ ፍረጃ እንደሌለው ጠቅሰዋል።
ይህንን ለመረዳት ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ያካሄደቻቸውን የ1966ቱን እና የ1983ቱን ሥር-ነቀል አብዮቶች ማየት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ሁለቱም አብዮቶች በአመጽ የተዋለዱ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ዘሪሁን፣ አብዮቶቹ የኢትዮጵያን ሀገራዊነት መከበርም ሆነ መቀጠል ከመንግሥት መኖር ጋር እንዳቆራኙት ተናግረዋል፡፡
እንደዚያ ዓይነቱ አፍርሶ መገንባት ደግሞ ኢትዮጵያ እሴት እየጨመረ የሚሄድ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት እንዳይኖራት ማድረጉን ነው አቶ ዘሪሁን ያወሱት።
መደመር ከዚያ አንጻር ሲታይ መጨመርን ግብ አድርጎ ለዚያ ደግሞ ምን ዓይነት መንግሥታዊ ቁመና እና አወቃቀር ቢኖር እና በምን ዘርፍ ቢያተኩር እየጨመረ እንደሚሄድ የሚያስቀምጥ እንደሆነ ጠቁመዋል።
መጽሐፉ ለይስሙላ ሳይሆን ታስቦበት የተጻፈ መሆኑን ያወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ማንም ሰው በዚህ ሰፊ እይታ ካልተመለከተው ትክክለኛውን ሀሳብ እንደማያገኝ ጠቁመዋል።
መፃፍ እንደ መናገር ቀላል እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ "መደመር አይነኬ ነኝ ብሎ ስለማይዘጋ፣ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መጽሐፉን አንብቡትና መዝኑት ብዬ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል፡፡
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #መደመር #YemedemerMengist