Search

"መደመር እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብሎ አይነሳም" - ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)

ሰኞ መስከረም 12, 2018 25

መደመር ያለፉትን መንግሥታት ሲያነሳ የእነርሱን ስህተት ነቅሶ ራሱን ብቻ ትክክል ለማድረግ ሳይሆን የነበሩ እጥረቶችን በጋራ ለመገምገም የሚጋብዝ መሆኑን የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

"መደመር ስላለፈው ሲያወራ ያለፈውን የማንቋሸሽ፣ ‘እኔ ብቻ ነኝ ልክ’፣ ‘እኛ አሁን መልሱን አግኝተናል’፤ ‘እነርሱ እኮ የሚረቡ አይደሉም፤’ በሚል አይደለም የተቀመጠው” በማለት ነው መደመርን ያብራሩት።

ከነገሥታቱ ጀምሮ እስከ ኢሕአዴግ ድረስ ያሉትን መንግሥታት ሲያነሳ በጥንቃቄ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ያሰቧቸው እና የሞከሯቸው ጉዳዮች ምን እጥረት እንደነበረባቸውም በጥንቃቄ እንደሚጠቁም ገልጸዋል።

እንደዚህ ዓይነቱ አቀራረብ ጤናማ መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ይህ ደግሞ መደመር ሊያመጣው ለሚያስበው ለውጥ እንደ ግብዓት የሚጠቅም እንደሆነ ተናግረዋል።

"መደመር አንድ ዓይነት የትረካ ሞኖፖሊ ይኑር፤ አንድ ወሳኝ ጥያቄ አለ፤ አንድ ትክክለኛ መልስ አለ፤ ብሎ አይሄድም" ሲሉ ገልጸውታል። 

መደመር እውነታውን በአንድ ዓይነት ብቻ እንደማይመለከት ጠቁመው፣ ክፍተቱን በማስረጃ ለመተቸት የሚመጡትን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነ ግምገማቸውን አስቀምጠዋል።

"የመጽሐፉ መሠረት ኃይማኖት፣ ሳይንስ ወይም ሞራሊቲ ላይ አይደለም" የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው፣ አቀራረቡም "እኔ እንደዚህ አቅርቤያለሁ፤ እናንተም በምክንያታዊነት ፈትሹኝ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

መደመር ፈላስፋውን ዘርዓ ያዕቆብን እንደሚያስታውሳቸው ጠቅሰው፣ “ዘርዓ ያዕቆብ መጨረሻ ላይ ‘እኔ አቅርቤያለሁ፤ ከኔ በኋላ የምትመጡ ደግሞ አክሉበት’ እንደሚለው ሁሉ መደመርም ሐሳቤ ሙሉ ስለሆነ መነካት የለበትም የሚል አይደለም” ብለዋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #YemedemerMengist