በውሃ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የደህንነት ስጋቶችን በብቃት ለመጠበቅ የተቋቋመው የባሕር ላይ እና ዳርቻዎች ጥበቃ ፖሊስ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ወንጀልን አስቀድሞ መከላከል እና ሲፈጸም በብቃት መመርመር የሚያስችል ዘመናዊ የፖሊስ ተቋም እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሥራውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ መካከል የውሃ አካላትን ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የባሕር ላይ እና ዳርቻዎች ጥበቃ (ኮስታል ጋርድ) የተሰኘ የፖሊስ ክፍል መደራጀቱን ጠቅሰዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ንጋት ሐይቅ ሥራ መጀመሩንም አስታውቀዋል።

ኮስታል ጋርድ ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎችን የታጠቀ መሆኑን በማንሳት፥ ጀልባዎቹ በሐይቆች እና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የደህንነት ሥጋቶችን መከላከል እና በብቃት ምላሽ መስጠት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮስታል ጋርድ አባላት በዘርፉ በቂ ስልጠና ያገኙ እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ዘመናዊ የሞተር ጀልባዎቹ የክትትል ካሜራዎች፣ የላቀ የመገናኛ ዘዴዎች እና የራዳር ሲስተም የተገጠመላቸው መሆናቸውን ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
ጀልባዎቹ በውሃ አካላት ላይ የሚፈጠሩ ማናቸውንም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች እና የደህንነት ስጋቶችን በብቃት መቆጣጠር እንደሚያስችሉም ነው የተናገሩት።
#Ethiopia #ሕዳሴግድብ #GERD