ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የማይገኝለት እጅግ አስደናቂ የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ብዝኃነት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቱሪዝም - አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተር” በሚል ባደረጉት ቃለመጠይቅ፣ ኢትዮጵያ ከ6 ሺህ በላይ ብርቅዬ የዕፅዋት ዝርያዎች እንዲሁም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሌሉ የዱር እንስሳት መገኛ የሆነች የዓለማችን "የተፈጥሮ ላቦራቶሪ" ናት ብለዋል።
ከባሕር ጠለል በላይ 4 ሺህ 620 ሜትር ወደ ሰማይ ከፍ ካለው የራስ ዳሽን ተራራ፣ ከባሕር ጠለል በታች 125 ሜትር እስከሚያዘቀዝቀው የዳሎል ምድር ያለው እጅግ ሰፊ የመልክዓ ምድር ልዩነት ለቱሪስቶች ልዩ መስህብ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህ አስደናቂ መልክዓ ምድር ውስጥም እንደ ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ እና ጥቁር አንበሳ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት እንዲሁም በባሌና በአዋሽ ብሔራዊ ፓርኮች የሚገኙ ማራኪ የአዕዋፍ ዝርያዎች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ውበት ይበልጥ ደማቅ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ በድንጋይ ላይ የተቀረጸ ሕያው ጥበብ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የጎንደር አብያተ መንግሥታትና የጎርጎራ ቅርሶች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙት የሶፍ ዑመር የተፈጥሮ ዋሻ፣ ጥንታዊ መስጊዶችና የሐረር ጀጎል ግንብ እንዲሁም በምዕራብ የጅማ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት የኢትዮጵያን ጥልቅ የታሪክ መሠረት እና ባለብዙ መልክነት አጉልተው የሚያሳዩ ውድ የቱሪዝም ሀብቶች መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ልጅ፣ የቡናና የጤፍ መገኛ መሆኗ ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ልዩ ትርጉም እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነው የዓድዋ ድል ባለቤትነትና በቅኝ ያልተገዛች ሀገር መሆኗ ደግሞ ኢትዮጵያን የታሪክና የነፃነት ተምሳሌት ያደርጋታል ብለዋል።
ይህን የድህነት ትረካ ቀይሮ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ቱሪዝም ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን በመገንዘብ፣ መንግሥት ዘርፉን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ እየሠራበት መሆኑን አንስተዋል።
ይህን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየርም ሆነ ኢትዮጵያን በልኳ ለማሳየት እያንዳንዱ ዜጋ በሀገር ገጽታ ግንባታ ላይ በጋራ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል።
በላሉ ኢታላ