Search

የቱሪዝም ዘርፍን የኢኮኖሚ ምሰሶ ያደረገው የመሠረተ ልማት አብዮት

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 42

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ‘ቱሪዝም - አዲሱ የኢኮኖሚ ሞተርበሚል ባደረጉት ቃለመጠይቅ ከለውጡ በኋላ የተመዘገበውን የቱሪዝም መሠረተ ልማት ሽግግር፣ ግንባታዎቹ የተከናወኑበትን አካሄድና ዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ስምምነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም ቀደም ሲል የነበረውን የቱሪዝም ማነቆ ለመስበር መሠረተ ልማት በአራት ዋና ዋና ምሰሶዎች ተከፍሎ የተቀናጀ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

እነዚህም የጉብኝት ስፍራዎችን ማልማት፣ የቱሪስቶች ማረፊያ የሆኑ ዘመናዊ ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን መገንባት፣ የትራንስፖርት አውታሮችን ማስፋፋት እና እንግዶች ሳይመጡ አስቀድመው መረጃ የሚያገኙበትንና አገልግሎት የሚይዙበትን የዲጂታል መሠረተ ልማት መዘርጋት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት ተግባራዊ የሆኑ የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን ከተሞች ገጽታና የከተማነት ደረጃ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ለአብነትም በአሁኑ ወቅት የተገነባው የእንጦጦ ቤተ ጊዮርጊስ ሙዚየም የገበታ ለሸገር አካል ሲሆን፣ ባህልና ጥበብን እንዲሁም የሀገር በቀል ምግቦችና የቡና ሥነ-ሥርዓትን ያካተተ አንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በአርባ ምንጭ፣ በጎርጎራ፣ በሐይቅ፣ በጅማ እና በጅግጅጋ (የሸበሌ ሪዞርት) የተገነቡት ግዙፍ ሪዞርቶችና የኮሪደር ልማቶች የየአካባቢውን ከተሞች የኢኮኖሚና የቱሪዝም እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ማነቃቃቱን አብራርተዋል።

ይህንን ስኬት ለማገዝም መንግሥት በቅርቡ ሰባት ተጨማሪ አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ሥራ ያስጀመረ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ እያንዳንዱ አዳዲስ የሪዞርት መዳረሻዎች የሚወስዱ ዘመናዊ የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ መሠረተ ልማቶች ተገንብተውላቸዋል ብለዋል።

ይህንን ግዙፍ ኢንቨስትመንት እውን ለማድረግ መንግሥት እጅግ ዘመናዊና የተለያየ የሀብት ማሰባሰቢያ ስልቶችን የተጠቀመ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የግሉ ዘርፍ በቀጥታ ገንዘብ በማዋጣት የተሳተፈበት የሕዝብና የግል አጋርነት መሆኑን ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግሉ ዘርፍ ገንዘብ በማዋጣት ብቻ ሳይወሰን፣ የመንግሥትን የላቀ ደረጃና የጥራት ምኞት ተከትሎ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ ኩሪፍቱ ያሉ ታዋቂ የግል ባለሀብቶች አሁን በአርባ ምንጭ የገነቡት ሪዞርት ከዚህ ቀደም ከነበራቸው አሠራር እጅግ የላቀ ደረጃና ውበት ያለው ሆኖ እንዲሠራ የመንግሥት አዳዲስ ግንባታዎች የደረጃና የጣዕም መለኪያን ከፍ ማድረግ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ሁለተኛውና እጅግ አስደናቂው አካሄድ የሕዝብና የመንግሥት አጋርነት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በተግባር የልማቱ ባለቤት መሆኑን አስረድተዋል።