Search

ባሕሩም ኢትዮጵያን ናፍቋል!

ረቡዕ ሰኔ 24, 2018 61

ታላቁ የፈረንሳይ መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት በአንድ ወቅት ስለ ቻይና ሲናገር፣ "Let China sleep, for when she wakes, she will shake the world" ("ቻይና ትተኛ፤ ስትነቃ ግን ዓለምን ታንቀጠቅጣለች") ማለቱ በታሪክ ይወሳል።

ይህ ጥልቅ አባባል እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለውን ነባራዊ ሁኔታም በብዙ መልኩ ይገልጻል።

የተኛችው ግዙፍ ሀገር መነሣት

ኢትዮጵያ ላለፉት ዘመናት በተደራረቡ የውስጥ ፈተናዎች፣ በጂኦፖለቲካዊ ሴራዎች እና በውስጣዊ ሽኩቻዎች ተተብትባ፣ ለጊዜው የአፍሪካ ቀንድ "የተኛች ታላቅ ሀገር" ሆና ቆይታለች።

ሆኖም የዝምታዋ ዘመን አብቅቶ፣ የታሪክ እና የተፈጥሮ ቦታዋን ዳግም ለመረከብ ከእንቅልፏ ነቅታለች፤ ታሪካዊ ጠላቶቿ የፈሩት አልቀረም፤ ተፅዕኖ መፍጠር ከምትችልበት ታሪካዊ እጥፋት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በቀጣናው እንዲሁም በአፍሪካ በኃያልነቷ፣ በልማት እና በዲፕሎማሲያዊ ስኬቶቿ የተፅዕኖ አድማሷን አስፍታለች። ብሪክስን ከመሳሰሉ ግዙፍ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፍ ስብስቦች አባል መሆኗም የሚነግረን ሐቅ፣ ኢትዮጵያ ከማንቀላፋት ምዕራፍ ወጥታ የአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር መሆን መጀመሯን ነው።

አዎ! የተኛችው ግዙፍ ሀገር ነቅታለች፤ ቀጣናውም የኢትዮጵያን ትንሣኤ እና የኃያልነት ኮቴ በጉልህ መስማት፣ አብሮ የማደግ ፍላጎቷንም ማድመጥ ጀምሯል።

የቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካዊ ስጋት

የቀይ ባሕር እና የባብ ኤል መንደብ የዓለም የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ ጉሮሮ በመሆኑ፣ በጂኦፖለቲካዊ ዕይታ ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስብ ወሳኝ ቀጣና ነው።

ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ይህ ስትራቴጂያዊ የውኃ አካል ቀድሞ የሚታወቅበት ሰላም እና መረጋጋት እየራቀው፣ የብዙ ኃያላን ሀገራት ዐይን ማረፊያ፣ የጂኦፖለቲካ መሻኮቻ፣ እንዲሁም የሽብርተኝነት እና የባሕር ላይ ወንበዴዎች የጥፋት ድግስ ስጋት ያጠላበት አደገኛ ቀጣና እየሆነ መጥቷል።

የቀጣናው ሰላም መደፍረስ የዓለም አቀፉን የንግድ ትሥሥር ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል። የሀገራት ኢኮኖሚ የሚሳለጥባቸው ታላላቅ የሸቀጥ ምልልሶች እና የንግድ ልውውጦች በስጋት ድባብ ውስጥ ወድቀዋል።

ለቀጣናው ባዕድ የሆኑ ኃይሎችም ጭምር በወደብ ችርቻሮ ምክንያት በአካባቢው የሚታዩበት እና አለቃ አልባ ሰፈር የሚመስል ሁኔታ የሚታይበት ሆኗል።

ይህ ሁሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምስቅልቅል ሊፈጠር የቻለው ዋነኛው ምክንያት፣ በዘመናት የፖለቲካ ሴራ የአካባቢው አሰባሳቢ ኃይል ኢትዮጵያ ከድንበሯ ተገፍታ፣ ቀጣናው አስተማማኝ ሰላም የሚያሰፍን ወሳኝ ኃይል ያጣ፣ "አለቃ አልባ" የሚሆንበት አጋጣሚ በመፈጠሩ ነው።

የዓለም አቀፍ ንግድ ጉሮሮ የሆነው የዚህ የባሕር በር አካባቢ ለተለያዩ የውጭ ኃይሎች በችርቻሮ የሚቀርብ፣ ለፖለቲካ ድርድር በእጅ መንሻነት የሚለገስ፣ ማንም የፈለገውን ጂኦፖለቲካዊ ቁማር እንዲጫወትበት ምቹ ከሆነ ሰነባብቷል።

ኢትዮጵያ - የቀጣናው ሰላም ዋስትና

በዚህ የተዘበራረቀ እና ስጋት በተሞላበት የጂኦፖለቲካ ማዕበል ውስጥ፣ ኢትዮጵያን የሚያክል ባለታሪክ፣ 130 ሚሊዮን በላይ ግዙፍ ሕዝብ ያላት እና ኃያል ሀገር ወደ ነባር ይዞታዋ፣ ወደ ባሕር መጠጋቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው አስተማማኝ ዘብ፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እጅግ ወሳኝ የሰላም እና መረጋጋት ዋስትና ነው።

ኢትዮጵያ የቀጣናው የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ምሰሶ ወይም "አንከር" ናት። የአፍሪካ ቀንድ የልብ ትርታ፣ የመረጋጋት ተምሳሌት እና የጂኦፖለቲካው ማዕከል ናት - ኢትዮጵያ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር የሕልውና ጥያቄዋ ምላሽ አግኝቶ ጠንካራ ተሳትፎዋን ካላረጋገጠች፣ የባሕር ላይ ሕልውና፣ የቀይ ባሕር እና የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ሁልጊዜም የተንጠለጠለ፣ በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ የሚበጠስ የሸረሪት ድር ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ጉዳይ ነው።

ሀገራችን ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ የባሕር ሉዓላዊነት ስፍራዋ ስትመለስ፣ ቀጣናው ለዘመናት የጎደለውን የሰላም ጠባቂ፣ የተረጋጋ የንግድ መስመር እና አስተማማኝ ዋስትና ያገኛል።

ትልቅ አቅም እንዳላት በተለያዩ ስኬቶቿ እያረጋገጠች የምትገኘው ኃያሏ ኢትዮጵያ በባሕር በሩ ላይ ማረፏ፣ አካባቢውን ከሽብርተኞች፣ ከሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እና ከውጭ ኃይሎች አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት በመታደግ የሁሉንም ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጽኑ መሠረት ይጥላል።

ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን በተግባር የምታሳየው ኢትዮጵያ፣ በቀጣናው ላይ ያላትን ተፈጥሯዊ የበላይነት እና የጠባቂነት ሚና ስትረከብ ብቻ ነው የባብኤል መንደብ ቀውሶች እውነተኛ እና ዘላቂ እልባት የሚያገኙት።

የታሪክ እና የተፈጥሮ ጥሪ

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል አቅሟን አጠናክራ፣ የያዘችውን ታላቅ ሕዝብ በአንድነት አንቀሳቅሳ፣ የተፈጥሮ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም በመጀመሯ፣ ክብሯን እና ዝናዋን እየመለሰች ትገኛለች።

በባሕር ላይ ሉዓላዊነትን ተጎናጽፋ የተፈጥሮ ቦታዋን ስትይዝ፣ የባሕር በር አካባቢ ሰላም እንደ አዲስ ይወለዳል፤ የሀገራት የንግድ ልውውጥም አስተማማኝ ዋስትና ያገኛል።

ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን የታሪክ እና ተፈጥሯዊ ትሥሥር ስንመለከት፣ በእርግጥም ባሕሩ ራሱ ኢትዮጵያን ይመኛል፤ ናፍቋታልም። ለዘመናት የጠበቀችውን፣ የተንከባከበችውን እና በክብር ያቆየችውን ኃያል እናት ሀገር ባሕሩ አጥብቆ ይሻል።

የተረጋጋ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን፣ ሰላማዊ የንግድ ዝውውርን እና ከሽብር ነፃ የሆነ ቀጣናን ለመፍጠር፣ የኢትዮጵያ እጆች ዳግም ባሕሩን ሊዳስሱ፣ መርከቦቿም ማዕበሉን ሊሰነጥቁ የግድ ይላል።

ይህ ፍላጎት የኢትዮጵያውያን የብሔራዊ ጥቅም እና የሉዓላዊነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጥሮ እና የጂኦፖለቲካ ሕግ የሚያስገድደው ሐቅ ጭምር ነው።

የባሕሩ ሞገድ የኢትዮጵያን መመለስ እያስተጋባ ይገኛል፤ ምክንያቱም ባሕሩ ያለ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ጥበቃ፣ ኢትዮጵያም ያለ ባሕሩ ሰፊ መተንፈሻ ሙሉ መሆን አይችሉምና። ሰላም ለጠማው ቀጣና፣ የኢትዮጵያን የባሕር ላይ ሉዓላዊ መብት ማረጋገጥ ብቸኛው እና የማይተካው መድኃኒት ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ