ለብዙ ዘመናት የአፋር ክልል በደረቅና ከፊል በረሃማ አየር ንብረቱ እንዲሁም በዋነኛነት በእንስሳት እርባታው ብቻ የሚታወቅ ነበር።
ይህ የተዛባ ትርክት ክልሉን ከምርትና ከበለፀገ ተፈጥሮ ይልቅ ከድርቅና ረሃብ ጋር አቆራኝቶት ነበር። ዛሬ ላይ ግን ይህ የተዛባ ትርክት ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል።
በአፋር በቅርብ ዓመታት የተጀመረው የግብርና አብዮት፤ ክልሉ ከዚህ ቀደም ሲታሰብበት ከነበረው ለየት ያለና ለም መሆኑን በተግባር ያሳየ ሆኗል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ በአፋር ክልልም የሚታይ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
በክልሉ ለዘመናት የቆየው ባህላዊ የእርሻ ዘዴ ተቀይሮ፤ አሁን ላይ በዘመናዊ የመስኖ ሥራዎች ሰፊ መሬት ወደ ለም ማሳነት እየተቀየረ ነው።
በክልሉ በተለያዩ ዞኖች በገቢ ረሱ፣ ማሂ ረሱ፣ አውሲ ረሱ፣ ኪልበቲ ረሱ፣ ፈንቲ ረሡ እና ሀሪ ረሱ የተጀመረው የክረምት ግብርና ይህንን ያሳያ መሆኑም ተገልጿል።
አርብቶ አደሮች፣ ከፈል አርሶ አደሮች እና አርሶ አደሮች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ምግብ ራሳቸው በማምረት በመቻላቸው፤ የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ላይም ይገኛሉ።
በታየው የምርት መጨመር አርብቶ አደሮች፣ ከፈል አርሶ አደሮች እና አርሶ አደሮች የገቢ ምንጫቸውን በማስፋት የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻልም ችለዋል። ይህ ደግሞ ለተሻለ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲሁም ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።ይህም የግብርና ምርት እመርታ የጎረቤት ክልሎችንም ጨምሮ ለሀገር አቀፍ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲጨምር አድርጓል።
በክልሉ ባሳለፍነው የክረምት ግብርና እንቅስቃሴ አማካኝነት እንደ ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ እንዲሁም የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በስፋት በመመረት ላይ ናቸው።