Search

ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት ሽግግር ተስፋን ፈንጥቋል፦ ዘጋርዲያን

ማክሰኞ መስከረም 13, 2018 158

በቅርቡ ለምርቃት የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት ሽግግር የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ተስፋ ፈንጥቋል ሲል ዘጋርዲያን በዘገባው አስነብቧል።
ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ መስጠቷ፣ የሀገሪቱን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ እና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር እንደገለጸው፤ በአሁኑ ጊዜ ወደ 115 ሺህ የሚጠጉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሀገሪቱ የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የቻይናው ቢዋይዲ ምርቶች ናቸው።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ ባረኦ ሀሰን "እጅግ ከፍተኛ ታዳሽ ኃይል አቅም አለን" ይላሉ።
የናፍጣ እና ቤንዚን ተሽከርካሪዎችን እንዳይገቡ ማገዱ በአረንጓዴ ፖሊሲዎች እና በዋና ከተማው የትራፊክ መጨናነቅ ወቅት ያለውን የአየር ብክለት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ነዳጅ ከውጭ ለማስገባት በዓመት ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። "ይህ ከዋና ዋና ወጪዎቻችን አንዱ ነው" ይላሉ ሚኒስትር ዴኤታው ባረኦ።
ይህ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚደረገው ፈጣን ሽግግር የራሱ ተገተዳሮቶች እንዳሉት ገለጸው፣ ከነዚህም ውስጥ የኃይል መቆራረጥ እንዲሁም የኃይል መሙያ ጣቢያዎች እጥረት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተለይ አሽከርካሪዎች ከከተማው ውጭ ለመጓዝ እንደሚቸገሩ ይገልጻሉ።
አሁን ባለው የዋጋ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ውድ ቢሆኑም፤ የግብር ቅነሳዎች እና በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራዎች መጀመራቸው ለወደፊቱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለነዚህ ችግሮች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት ሽግግር የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ተስፋን ፈንጥቋል ሲል ዘጋርዲያን በዘገባው አስፍሯል።
በሰለሞን ገዳ