Search

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት ረገድ የጎላ ፋይዳ አለው፡- ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 69

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ከማሳካት ረገድ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አናሌና ቤርቦክ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በወቅታዊ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ እያሳረፈ ስላለው ተጽዕኖ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
በውይይቱ ፕሬዚዳንት ታዬ፣ የባለብዙ ወገን ግንኙነትእና የጋራ ደኀንነት መርሆዎችን ለማስጠበቅ የጋራ ጥረቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በቅርቡ የተመረቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት፤ የተመድ ዘላቂ ልማት ግቦችን ከማሳካት ረገድ በተለይም ግብ 7ን ለማሳካት ግድቡ ንጹህ የኃይል አቅርቦት ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
መሰል ፕሮጀክቶች ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮችን የበለጠ ለማጠናከር መልካም ዕድል ይዘው የሚመጡ መሆናቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።
የጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንት አናሌና ቤርቦክ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር መርሆችን ማክበር እና መጠበቅ ለዓለም ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ልማት፣ ቀጣናዊ ሰላም እና ደኀንነትን ጨምሮ በተለያዩ ቀጣናዊ የትኩረት መስኮች ላይም መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።