Search

የብዙዎችን እንግልት እና ድካም የቀነሰው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 51

በአዳማ ከተማ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እያስቻላቸው መሆኑን ተገልጋዮች ገለጹ።

ተገልጋዮች እንዳሉት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረን ከአንዱ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም ጉዳይን ለማስጨረስ  የነበረን የጊዜ ብክነት አስቀርቷል።

ከተገልጋዮቹ  መካከል አቶ መሀመድ አብዱልጀሊል በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ አገልግሎት አሰጣጡን  ለማሻሻል የተገበረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በማቀናጀት ጊዜና ገንዘብን መቆጠብ  ማስቻሉንም ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በተለይ ጉዳይ እናስጨርሳለን በማለት ህብረተሰብን ለተጨማሪ ወጭ የሚዳርጉ ደላሎች እና ሙሰኞችን ያስቀረ መሆኑንም አስረድተዋል። 

ሌላኛው ተገልጋይና የቦኩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ከዚህ በፊት ከአስተዳደሩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ረጀም ቀጠሮና መጉላላት ይደርስባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ  አሁን በተግባር ላይ የዋለው  መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መፍትሄ መስጠቱን ተናግረው  ከመሬት ይዞታ ጋር የተያያዙ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም 30 ደቂቃ ውስጥ መስተናገዳቸውን አስረድተዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላ ቢሮ በታክሲ በመጓጓዝ የነበረውን እንግልት አስቀርቶልናል የሚሉት ደግሞ የኢንቨስትመንት መሬት ጉዳይ ለማስጨረስ በማከሉ ያገኘናቸው አቶ ቱሉ አንበሴ ናቸው።

በአገልግሎት አሰጣጡ የአመራሮች እና ባለሙያዎች  አገልግሎት ፈጣን በመሆኑ በየደረጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ መኩሪያ ድንቁ፥ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ቀልጣፋና ፍትሃዊ እንዲሁም ግልፀኝነት ያለው አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህብረተሰቡ  የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የመሬት አስተዳደር፣ ኢንቨስትመንትና ገቢዎችን ጨምሮ 138 አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።

ማዕከሉ ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል በማስገባት የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት ማስቻሉንም ተናግረዋል።

ይህም ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ሥራዎችን ከማስቀረቱም በተጨማሪ ማንኛውም ተገልጋይ ባለበት ሆኖ በኦን ላይን ሲስተም ጉዳዩን ማስጨረስ እንደሚችል አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡ ከተደራሽነት ረገድ በወረዳና በክፍለ ከተሞች ተመሳሳይ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲዘረጋለት መጠየቁን ተከትሎ ይህንን የሚያስፈጽም የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም 45 ቀናት ውስጥ በታችኛው እርከን ላይ አገልግሎቱን ለማስጀመር መታቀዱን አብራርተዋል።