Search

ኢትዮጵያን የዘመናዊ ከተሞች ባለቤት የማድረግ ጥረት

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 52

ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው የፖሊሲ አሰራር በገጠር ግብርናው ላይ ያተኮረ ስለነበር የከተሞችን እድገትና ልማት የዘነጋ የረጅም ጊዜ እድገታቸውን ታሳቢ ያላደረገ ነበር ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን ገለጹ፡፡

ችግሩን ከስር መሰረቱ በመረዳት የመደመር መንግስት ለከተሞችም ሆነ ለገጠር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ከተሞች ለሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት 50 ከመቶ ድርሻ ቢኖራቸውም ለኢኮኖሚው በሚያበረክቱት ልክ ከልማቱ ተጠቃሚ አልነበሩም የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ልማቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ የእግረኛ፣ የሳይክልና የተሽከርካሪ መንገዶች አንድ በመሆናቸው በህይወትና በንብረት ላይ አደጋ ያስከትል እንደነበር አስታውሰው፤ ይህን ነባራዊ ሀቅ ለማስቀረት የሚያስችል ስራ በከተሞች ተሰርቷል ብለዋል፡፡

ነባሩ የከተሞች አወቃቀርና ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ያልሆነ እና የተጨናነቀ፣ ለህጻናትና  ለአረጋዊያን ምቹ ያልነበረና ለአደጋ አጋላጭ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለነዋሪዎች ምቹ ከተሞችን ለመገንባት በተደረጉ ጥረቶች ጉድለቶችን በመለየት ውጤታማ የልማት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ሰጪነት የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ውጤት ማምጣታቸውን የመደመር መጽሐፍን ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሚኒስትሯ የፖሊሲ አማካሪ / ያሬድ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን የዘመናዊ ከተሞች ባለቤት ለማድረግ በተለምዶ ሲሰራ ከነበረበት እሳቤ በመውጣት በተለየ መንገድና አሰራር ዘመናዊና ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እየተሰራ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

65 ከተሞች ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎች ሰው ተኮርና ውጤታማነታቸው በህብረተሰቡ ዘንድ የተመሰከረላቸው ናቸው ብለዋል፡፡

በከተሞች ያረጁና ያፈጁ ሰፈሮች ላይ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ነዋሪዎች ተጨናንቀው ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለዜጎች ቅድሚያ በመስጠት ምቹና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮችን ገንብቶ በመስጠት ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ላይ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ስራዎች ከተማዋን እጅግ ውብና ማራኪ በማድረግ ለነዋሪው ምቹ ከተማዋን ብሎም ፅዱ የሚያደርግ መሆኑን አማካሪው ገልጸዋል፡፡  

በመሐመድ ፊጣሞ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Corridor_development #modern_city