Search

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 48

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ ብጹዕ አቡነ ዲዎስቆሮስ እንዲሁም የአ/ አገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ እና የመስቀል በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ በተገኙበት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ከከተማዉ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት  እና በከተማዉ አስተዳደር በሚደረገዉ ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል። 

የመስቀል ደመራ በዓል መስቀል አደባባይን ጨምሮ 2375 ደብሮችና ቦታዎች ላይ የሚከበር መሆኑ በመጥቀስ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን እና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በደመቀና ባማረ መልኩ እንዲከበር፤ የከተማዉ አስተዳደር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመግለፅ  አባቶች እና የኮሚቴዉ አባላት እየተደረገ ላለዉ ድጋፍ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል። 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የበዓሉ ዋና ባለቤትና በዓሉን የምትመራዉ የምታስተባብረዉ የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ብትሆንም የመስቀል ደመራ በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝብ በአደባባይ የሚያከብረዉ የአገር ሀብት ፣የከተማችን ድምቀት እንዲሁም የቱሪዝም መስህብ  ነዉ ብለዋል።

በዓሉ ሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እንዲከበር፤ እንዲሁም አብሮትን በሚያጠናክር መልኩ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሌሎችም የአደባባይ ክብረ በዓላት የሚያደርገዉን ድጋፍ የከተማዉ አስተዳደር እያደረገ ይገኛልም ብለዋል ከንቲባዋ።