Search

ጣና ሐይቅና አካባቢው በዚህ ዓመት በዩኔስኮ ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 48

በጣና ሐይቅና አካባቢው ያሉ የባህልና የተፈጥሮ መካነ-ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።

ቢሮው ጣና ሐይቅ እና በዙሪያው ያሉ ደሴቶችን በባህላዊና ተፈጥሯዊ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑን ነው የገለፀው።፡፡

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ባለፉት ሁለት አመታት ጣና ሐይቅን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።

ጣና ሐይቅን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ጋር በጋራ በመሆን ጥናት ተደርጎ ለዩኔስኮ የተላከ ሲሆን ጥናቱ ተቀባይነት አግኝቷል ነው ያሉት።

ዩኔስኮ በያዝነው ዓመት በደቡብ ኮሪያ በሚያካሂደው 48ኛው የዩኔስኮ ጉባኤ ላይ ጣና ሐይቅ በዓለም ቅርስነት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በተደረገው ጥናት መሠረት የዩኔስኮ ባለሞያዎች የተላኩ መረጃዎችን ተመልክተው ጣና ሐይቅ እና አጠቃላይ ሀብቱ ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት በመስከረም ወር መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ኃላፊው ገልፀዋል።

ባለሞያዎቹ በቆይታቸው በሚያደርጉት ጉብኝት የአካባቢውን ማህበረሰብ ካወያዩ እና ጥናት ካደረጉ በኋላ ተመልሰው በሚያቀርቡት ሪፖርት መሠረት ቅርሱ ዩኔስኮ ላይ ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ከዚህ ቀደም የጎንደር አብያተ መንግስታት፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው ይታወቃል።

በሔለን ተስፋዬ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #LakeTana #UNESCO