ላለፉት ዓመታት ሲተገበር የነበረው የሪሜዲያል (አቅም ማሻሻያ) ፕሮግራም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስደው ማለፊያ ነጥብ ማምጣት ያልቻሉ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡበትን ዕድል ማመቻቸቱን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የሪሜዲያል ፕሮግራሙ መንግሥት ለትምህርት ጥራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበትም ነው ሲሉ በሚኒስቴሩ የአስተዳደር እና መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃም (ዶ/ር) ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ አገር አቀፍ ፈተና ወስደው ማለፊያ ነጥብ ማምጣት ያልቻሉ ተማሪዎች ለአንድ ተጨማሪ ዓመት በሚሰለጥኑበት በዚህ ፕሮግራም በአገር አቀፍ ፈተናው ካለፉ ተማሪዎች 3 እጥፍ የሚሆኑ ተጨማሪ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ የማብቃት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
የሪሜዲያል ፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በሁሉም አማራጮች (በግል እና በመንግሥት ተቋማት) ፕሮግራሙን ከተከታተሉ በኋላ የሚፈተኑትን ፈተና ከ50 በመቶ በላይ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የሪሜዲያል ፕሮግራሙ ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት በዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ወደ ፕሮግራሙ ለሚገቡ ተማሪዎች ስልጠና የመስጠት ሥራው የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ባማከለ መልኩ ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ብቁ፣ በራሱ የሚተማመን እና በየትኛውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት መንግሥት በቀረፀው ፖሊሲ መሠረት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBCdotstream #MoE #RemedialProgram