Search

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ታላቅ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 43

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ከ62 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ዛሬ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው ወታደራዊ ስምምነት እ.ኤ.አ በ1963 ኬንያ ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ ከተፈራረሙት ቀጥሎ መከላከያ ለመከላከያ የተደረገ ታላቅ ወታደራዊ ስምምነት ነው።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የኬንያ መከላከያ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው መስኮች ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ወታደራዊ የትብብር ስምምነቱ እንደሌሎች ስምምነቶች የሚታይ ሳይሆን፣ ስትራቴጂያዊ በሆኑ ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችል፤ ሀገራት በመካከላቸው ያለው ግንኙነትና መተማመን በሚያድግበት ወቅት የሚፈፀም ነው።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኬንያ  የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኬንያና የኢትዮጵያ መከላከያ ተቋማት በተለያዩ ወታደራዊ መስኮች በትብብር እየሠሩ መምጣታቸውን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ በቀጣይም በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለፁት።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ ከኬንያ መከላከያ ኢታማዦር ሹም ጋር በወታደራዊ መረጃ ልውውጥ፣ በጋራ ወታደራዊ ልምምድ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ ስልጠና፣ ሽብርተኝነትን በመዋጋት፣ በድንበር ደህንነት እና በሌሎችም ተያያዥነት ባላቸው ወታደራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተፈራርመናል ብለዋል።

በተጨማሪም በስምምነቱ መሠረት ከሀገራቱ በተጨማሪ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ በጎ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በርካታ ሥራዎችን አብረን እንሠራለን ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

የኬንያ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርልስ ሙሪዩ ካሃሪሪ በበኩላቸው፥ ለእርሳቸው እና ለልዑካን ቡድናቸው ለተደረገላቸው ደማቅ እና የሞቀ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

አክለውም፥ የኢትዮጵያ እና የኬንያ ግንኙነት ከታሪክም ባለፈ በባህል፣ በህዝብ ለህዝብ እና በጂኦግራፊ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ያደረጉት ወታደራዊ ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋትም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ጄኔራል መኮንኑ ገልፀዋል።

ለወደፊትም ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር በትብብር በሚሠሩ ሥራዎች ዙሪያ የኬንያ መከላከያ ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጣቸውን የመከላከያ ሚዲያ ዘገባ ያመለክታል።

#EBCdotstream #Ethiopia #Kenya #DCA #ENDF #KDF