Search

የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን መቋቋም ተስኗት ልትጠፋ የተቃረበችው በዓለም ሶስተኛዋ ትንሿ ሀገር

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 37

80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መደበኛ ስብሰባ በኒውዮርክ እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ መሪዎች የዓለም አሁናዊ ሁኔታዎችን በንግግሮቻቸው ዳስሰዋል።

ዓለም በአሁኑ ጊዜ "መስቀለኛ መንገድ ላይ ናት" የሚያስብላት ከባድ ፈተናዎችን እየጠጋፈጠች ትገኛለች። እነዚህ ፈተናዎች ሰው ሠራሽ እንደመሆናቸው፤ መፍትሔዎቹም ሰዎች ጋር ቢሆኑም፣ ዓለም ግን ችግሮቹን ለመፍታት ዳተኛ ሆኗል።

የዓለም ፈተናዎች የሚባሉት ሁሉ በየዓመቱ በሚካሄዱት የተመድ መደበኛ ጉባኤዎች ላይ እየተነሱ ዓለም የጋራ መፍትሔ እንዲሰጥባቸው ቢጮህም፤ እስከ አሁን የመጣ ለውጥ ግን የለም።

የሩስያ-ዩክሬን ጦርነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ፣ የቀይ ባሕር ውጥረት እና በየሀገራቱ የሚፈጠሩ የውስጥ እና ድንበር ዘለል ቀውሶችን በተባበረ ክንድ ለመፍታት ጥሪ ቢደረግም፤ ጠብ ያለ የመፍትሔ ተግባር ግን የለም።

ዓለም እርስ በርስ መቆራቆሱ ሳይበቃው የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ ሌላ ፈተና የደቀነ አስፈሪ ጉዳይ እየሆነበት መጥቷል። በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው 80ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና አንዱ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በመክፈቻ ንግግራቸው፥ ዓለም ተደራራቢ ቀውሶች እያጋጠሟት መሆኑን ጠቅሰው፤ ያለ ዓለም አቀፍ ትብብር ፕላኔቷ "ትርምስ" እንደሚገጥማት አስጠንቅቀዋል። ወደ ታዳሽ ኃይል የሚደረግ ሽግግር ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ያሰመሩበት ዋና ጸሐፊው፤ ሀገራት አዳዲስ እና ድፍረት የተሞላባቸው የአየር ንብረት ዕቅዶችን እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP30) አዘጋጅ የሆነችው ብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ፥ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እውነተኛ ትብብር ሊያሳይ እንደሚገባው አሳስበዋል። በቤሌም የሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ (COP30) "እውነተኛ የአየር ንብረት ጉባኤ" እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፤ ጉባኤው የዓለም መሪዎች ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሆን አለበት ብለዋል። ዓለም ለታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ አረንጓዴ ፕሮጀክቶች ቃል የተገባውን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የአየር ንብረት ፍትህን ተግባራዊ እንዲያደርግም ነው ዳ ሲልቫ ጥሪ ያቀረቡት።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፥ የአየር ንብረት ለውጥ ለአፍሪካ የሕልውና ስጋት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአህጉሪቱ ልማትን እያቀጨጨ፣ ድህነትን እና አለመረጋጋትን እያባባሰ ነው ሲሉ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል። ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ዓለም በአፍሪካ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉ የታዳሽ ኃይል እና አረንጓዴ ልማቶችን በመደገፍ የአየር ንብረት ፍትህን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ካሉት መሪዎች መካከል የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ኑማ ቦካይ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የደቀነውን ፈተና ዘርዝረዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናን ለመቋቋም ሀገራዊ ጥረቶች እንዳሉ ሆነው የጋራ መፍትሔም የግድ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። "የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ የሩቅ ስጋት ሳይሆን አሁን ያለ እውነታ ነው፤ ፈተናውን ለመቋቋም የተናጠል ጥረታችን ብቻ በቂ አይደለም" በማለት አክለዋል። "ከሁሉም በላይ የአየር ንብረት ፍትህ እንዲኖር እንጠይቃለን፤ ለዚህ ቀውስ አነስተኛ አስተዋፅዖ ያደረገችው አፍሪካ ከዚህ በላይ መሰቃየት የለባትም" በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል።

የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንት ፕራቦቮ ሱቢያንቶ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በደሴቷ ሀገራቸው ላይ እያመጣው ስላለው ቀጥተኛ መዘዝ ተናግረዋል። የባሕር ከፍታ እየጨመረ መምጣቱን እና ኢንዶኔዥያም ዋና ከተማዋን በባሕር ከመጥለቅለቅ ለመጠበቅ ግዙፍ የባሕር ግንብ እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው ስለ አየር ንብረት ለውጥ ያነሱት የኢራቁ ፕሬዚዳንት አብዱልለጢፍ ጀማል ረሺድ ናቸው። ፕሬዚዳንቱ የአየር ንብረት ለውጥ ቱርክ፣ ኢራን እና ሶሪያ በሚጋሩአቸው የኢፍራጠስ እና ጢግሮስ ወንዞች ተፋሰሶች ላይ የደቀነውን ፈተና አንስተዋል። ይህን ፈተና ለመከላከል እና ወንዞቹ እንዳይደርቁ ለማድረግ የጋራ ጥረት እንሚያስፈልግ ነው ፕሬዚዳንቱ ጥሪ ያቀረቡት። አክለውም "ምድራችንን ለመፈወስ፣ ወንዞቻችንን ለመጠበቅ፣ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ፣ ወጣቶቻችንን ለማበረታታት እና የቀጣናዎቻችንን አንድነት ለማረጋገጥ በጋራ እንሰለፍ" ብለዋል።

የናኡሩ ሪፐብሊክ በመካከለኛው ፓሲፊክ ውቅያኖስ ደሴት ላይ የምትገኝ እጅግ በጣም ትንሽ አገር ናት። ናኡሩ በዓለም ሶስተኛዋ ትንሿ ሀገር ስትሆን፤ በፎስፌት ማዕድን ቁፋሮ በደረሰው ከፍተኛ የአካባቢ ጉዳት ምክንያት የደሴቲቱ አብዛኛው ክፍል ቋጥኝ የበዛበትና ለመኖሪያነት የማይመች በረሃ ሆኗል። የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዴቪድ አዲያንግ በ80ኛው የተመድ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። እርሳቸው እንዳሉት፥ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያጠፋቸው ከደረሰ አገራት አንዷ ናኡሩ ናት። ደሴቲቱ የአየር ንብረት ለውጥ የጋረጠባትን ጫና እና ኢኮኖሚያዊ ፈተና መሸከም አልቻለችም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። "የአየር ንብረት ለውጥ የአካባቢ ቀውስ ብቻ አይደለም" ያሉት ፕሬዚዳንት አዲያንግ፤ "ለሰላማችን፣ ለደህንነታችን እና ለሕልውናችን ቀጥተኛ ስጋት በመሆኑ፣ ለመፍትሔው መሥራት ለሌላ ጊዜ መባል የሌለበት ጉዳይ ነው" ብለዋል።

 

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፥ ከዓለም የአየር ንብረት እርምጃ ጥሪዎች ጋር በእጅጉ የተቃረነ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። "የአረንጓዴ ኢነርጂ አጀንዳ በዓለም ላይ እስካሁን ከተፈፀሙ ትላልቁ የማጭበርበር ሥራዎች አንዱ ነው" በማለት የመሪዎቹን የአየር ንብረት እርምጃ ጥሪ ተችተዋል። ትራምፕ በንግግራቸው በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች ላይ ቀዝቃዛ ውኃ በመቸለስ "ቅድሚያ ለአሜሪካ" የሚለውን አጀንዳቸውን አንጸባርቀዋል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #climatechange #UNassembly #Cop30