Search

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

ረቡዕ መስከረም 14, 2018 23

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቢያንስ ሁለት ቋሚ መቀመጫ እና ሁለት ቋሚ ያልሆነ ውክልና ሊኖራት ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ እያደገች ያለች አህጉር መሆኗን ያነሱት ፕሬዚዳንት ሩቶ፤ አህጉሪቱ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ላይ ያላት ሚናም ማደግ እንዳለበት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ላይ ያነሱት ሌላው ሀሳብ የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ ሲሆን፤ በዚህም የዘመናችን ትልቁ ስጋት የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ስር ነቀል የፖሊሲ እርምጃ ይሻል ብለዋል።

አፍሪካ አሁን ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ብቻ ሳትሆን የመፍትሔ ምንጭ እየሆነች ነው፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንቶች ላይ እየተሰማሩ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በግድም ቢሆን ወደ መፍትሔው እንድገባ አድርጎናል፤ ውጤታማነቱን ደግሞ እያየነው እንገኛለን ነው ያሉት።

አፍሪካ በፋይናንስ ዙሪያ በአህጉሪቱ ትልቅ ሚና ያላቸውን የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የአፍሪካ ማዕከላዊ ባንክን የማጠናከር ሥራ እያከናወነች እንደምትገኝም አንስተዋል።

በሀብተሚካኤል ክፍሉ

#EBCdotstream #UNGA # WilliamRuto