ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ከ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን አፍሪካን በኤሌክትሪክ ለማዳረስ ዓላማ ያደረገውን “ተልዕኮ 300" ኢነርጂ ኢኒሼቱቭ ላይ ተሳትፈዋል።
ኢትዮጵያ ተልዕኮውን መቀላቀሏ እያካሄደችው ያለውን የኢነርጂ ማሻሻያ የሚያጎላ ዕውቅና በመሆኑ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በዓለም ባንክ ቡድን እና በሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች የሚደገፈው "ተልዕኮ 300" ኢነርጂ ኢኒሼቲቭ እስከ 2030 ድረስ በ50 ቢሊዮን ዶላር 300 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር በታንዛኒያ በተዘጋጀው “ተልዕኮ 300” ኢነርጂ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ ላይ ቡድኑ ውስጥ እንድትካተት አመልክታ ነበር።
ለአባልነት የሚያበቃትን ስትራቴጂ እና የትግበራ የጊዜ ሰሌዳዎችን በማዘጋጀት ቁርጠኝነቷን በድጋሚ ለማረጋገጥ የገባችውን ቃልም በተግባር አረጋግጣ ኢኒሼቲቩን መቀላቀሏ ታውቋል።
ኢትዮጵያ ኢነርጂን ለማዳረስ ትልቅ ዓለማ ይዞ የተነሣው "ተልዕኮ 300" አባል መሆኗ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተደራሽነቷን እንደሚያሳድግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ይህ የኢነርጂ ‘ኮምፓክት’ የኢትዮጵያን ሰፊ የታዳሽ ኃይል አቅም ሥራ ላይ ለማዋል ቀጣናዊ የኃይል ትሥሥርን እንደሚያሰፋ ተጠቅሷል።
ይህ ስኬት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የንፁህ ኢነርጂ ትራንስፎርሜሽን ውስጥ ያላትን ሚና ከማጠናከር ባለፈ የአህጉሪቱን የኃይል እጥረት በመቅረፍ እና ዘላቂ ልማትን ለማጎልበት እንደሚያበረታታ ታውቋል።
በለሚ ታደሰ