Search

አፍሪካን ያነቃቃው የኢትዮጵያ የኒውክሌር ፕሮጀክት ዕቅድ

ሓሙስ መስከረም 15, 2018 836

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ማበልፀጊያ የበርካታ ኃያላን ሀገራትንም ቀልብ ስቧል ሲል ዘገባውን የጀመረው አፍሪካን ቱዴይ በተሰኘው ሚዲያ ጥንቅሮቹን በዩቱዩብ የሚያቀርበው አሶንድዌድ ሉዊስ፤ ፕሮጀክቱ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ጭምር ትሩፋትን ይዞ የሚመጣ መሆኑን ነው ያነሳው።

ኢትዮጵያ በዚህ ፕሮጀክት መላው አፍሪካን በኒውክሌር ኃይል ልማት አንቅታለች ሲል ገልፆ፤ 10 የአፍሪካ ሀገራትም በኑክሌር ልማት ድርድር ላይ መሆናቸውን ነው ያስታወቀው።

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (/) ከተገለፁት 7 የጉባ ብስራቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የኒውክሌር ማበልፀጊያ፤ አፍሪካ የኑክሌር ቴክኖሎጂን ለመቀላቀል ከምዕራባውያን ፈቃድ እንደማያስፈልጋት ያረጋገጠ ነው ሲልም ገልፆታል።

አፍሪካ ዩራኒየምና የተለያዩ ለኃይል አቅርቦት የሚረዱ የተፈጥሮ ሃብቶቿ ወደ አውሮፓ እየተጋዙ ሕዝቦቿ ግን በጨለማ ውስጥ ለዓመታት ኖረዋል ይላል ዘገባው።

ፈረንሳይ 50 ዓመታት የኒጀርን ዩራኒየም በመውሰድ ለሀገሯ ልማት እና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቅማበታለች፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኒጀራውያን ግን ያለ ብርሃን አሁንም ጨለማ ውስጥ መሆናቸውን በቁጭት ያነሳል።

አፍሪካ ዩራኒየምን ማውጣት ብትችልም ልትጠቀምበት ፈጽሞ አልቻለችም፤ የኢትዮጵያም ዕቅድ ይህንን ሥርዓት የሚፈታተን ነው ብሎታል አሶንድዌድ ሉዊስ።

ቅኝ ባለመገዛት ለጥቁሮች ፋና ወጊ የሆነችው ኢትዮጵያ ግን "ከእንግዲህ ወዲያ ይህ ፈጽሞ መሆን የለበትም" ብላ የራሷን ሃብት በራሷ አቅም በማልማት አሳይታለች ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ የኒውክሌር ፕሮጀክት አፍሪካ በቴክኖሎጂ የበታችነትን እንደማትቀጥል ያመላከተ መሆኑንም ነው ያስረዳው። 

ይህ ፕሮጀክት ከመቶ ዓመታት በላይ በምዕራባውያን ተይዞ የቆየውን የቴክኖሎጂ ቁጥጥር ሥርዓት የሚገዳደር እና ለአፍሪካ ተስፋ ሰጪ ልማት ነው ሲልም ገልፆታል።

ወጣት አፍሪካውያን በተለያዩ ሀገራት በዘርፉ ዕውቀት እየቀሰሙ መሆኑን ጠቁሞ፤ የኢትዮጵያ እርምጃም በአፍሪካ የኒውክሌር ምርምር ማዕከላት፣ የኒውክሌር ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲሁም የኒውክሌር ኩባንያዎች ለመፍጠር አንድ ርምጃ የሚያራምድ መሆኑንም አመላክቷል።

ይሁንና ይላል ዘገባው፣ የኒውክሌር ፕሮጀክቶች በዓለም ዙሪያ አስቸጋሪ ታሪክ አላቸው። ከበጀት በላይ ወጪን መጠየቅ፣ መዘግየት፣ የቴክኒክ ችግሮች እና ሌሎችም የፖለቲካ ጫናዎች ሲያጋጥማቸው መስተዋሉን አንስቷል።

ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ፈተና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና በሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወቅት በተግባር አይታዋለች ሲልም ያነሳል።

በመሆኑም ለሰላማዊ ዓላማ የሚውለው የኢትዮጵያ የኒውክሌር ፕሮጀክት ስኬት አፍሪካ በዘርፉ ለምታቀናው ቀጣይ ሥራ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑን ገልጿል።

ስኬቱም ኢትዮጵያን በታዳሽ እና ያልተገደበ ኃይል የምትሰራ የኢንዱስትሪ ማዕከል ያደርጋታል ሲልም የአፍሪካን ቱዴይ ዘገባ ሰፊ ሃተታ አቅርቧል።

በጌትነት ተስፋማርያም