በ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ (UNGA) ላይ እየተሳተፉ ያሉ መሪዎች ዓለም ለገባችበት የሰላም ችግር እንድትወጣ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሁሉም ወገን ከትርምስ፣ መገለል እና የተናጠል ጥቅም ይልቅ ሁለገብነትን፣ ሕግን ማክበር እንዲሁም ትብብርን እንዲመርጡ ጥሪ ቀርቧል።
"በአንድነት የተሻሉ 80 ዓመታት፡- ለሰላም፣ ልማት እና ሰብአዊ መብቶች የበለጠ መሥራት" በሚል ጭብጥ እየቀረበ ያለው የመሪዎች ንግግር አሁን ያለውን የጂኦፖለቲካዊ ቀውስ ለመፍታተት የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በትክክል ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት መሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በንግግራቸው፣ "ከጦርነት ይልቅ ሰላም፣ ከኃይል አማራጮች የዓለም ሕግ በትክክል ይተግበር” በማለት አሳስበዋል።
በጋዛ፣ በዩክሬን እና በሱዳን እየተደረጉት ያሉ ጦርነቶች ዓለም አቀፍ ሕግ ችላ መባሉን ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ለሰው ልጆች ኅልውና ዓለም አቀፍ ትብብር በፍጥነት ተግባራዊ መደረግ አለበት ብለዋል።
750 ዶላር ለእያንዳንዱ የጦር መሣሪያ ወጪ እየተደረገ መሆኑን የጠቀሱት ጉቴሬዝ፣ ይህም ዓለም ለጦርነት የሚያወጣው ወጪ ለሰላም እና ልማት ከሚያወጣው ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።
የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በርካታ መሪዎች እውነተኛ ሰላም በዓለም ላይ እንዲሰፍን የመንግሥታቱ ድርጅት ትብብርን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተመሠረተ ከ80 ዓመታት በኋላ ዓለም እምነት እያጣብን ነው" ያሉት ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፉ ሥርዓት ላይ ጥያቄ የሚያስነሣ እና የድርጅቱን ግጭት የመፍታት አቅምን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ፐሬዚዳንት ራማፎሳ በበኩላቸው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል አባላት የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ መፍታት የሚችሉበት እንዲሆን ጠይቀዋል።
“ዓለም የልማት ግቦችን ለማሳካት ቅድሚያ ሊሰጥ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ ወጪን መጨመር የሞራል ድቀት ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንት ራማፎሳ።
አክለውም፣ "የልማት መሠረተ ልማቶችን መገንባት ሲገባን የጦር መሣሪያ እያመረትን ነው፤ ድህነትን መዋጋት ሲገባን ጦርነቶችን እየተዋጋን ነው" በማለት ዓለም ከሰላም ይለቅ ለግጭቶች ቅድሚያ መስጠቱን ኮንነዋል።
በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ቀውስ ሰላማዊ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ መሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ሰላም ከሰብአዊ መብቶች፣ ከፍትሕ እና ከልማት የማይነጣጠል መሆኑንም ነው መሪዎቹ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት።
የተቀናጀ የሰብአዊነት፣ የልማት እና የሰላም ጥረቶች መረጋጋትን እና ከግጭት በኋላ ለማገገም ወሳኝ መሆናቸውን መሪዎቹ በየንግግሮቻቸው ትኩረት ሰጥተውበታል።
መሪዎቹ ከአየር ንብረት ለውጥ እስከ ማባሪያ አልባ ግጭቶች ድረስ ያሉ ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የግል ጥቅምን ወደ ጎን በመተው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር ውስጥ የተካተቱትን የጋራ ደኅንነት እና ዓለም አቀፍ አስተዳደር መርሆዎችን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚለውን መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተመድ ዋና ጸሐፊው ጋር ባደረጉት ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላምን ለመፍጠር እየሠራ ያለውን ሥራ እንደሚያደንቁ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #EBC #UN #UNassembly #UNCharter