ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመከላከያ ሠራዊትም በገንዘቡ፣ በላቡ እና በደሙ ዋጋ የከፈለበት ድርብ የልማት ድል መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ እና የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ፤ የሕዳሴ ግድብ ስኬትና የሠራዊቱን ተሳትፎ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድረገዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵውያን የገንዘብ፣ የጉልበትና መሰል ያልተቆጠበ ድጋፍ ለስኬት መብቃቱን ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያውያን አብራክ የወጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊትም የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ግንባታው እንዳይደናቀፍ የከበረ መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግረዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት መንገድ በመገንባት የግንባታ ቁሳቁስ በማጓጓዝ በስኬት መጠናቀቁ ለሠራዊት አባላቱ ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ የልማት ድል መሆኑን አንስተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው፤ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውሉ ንብረቶች በሚያልፍበት አካባቢ ሠራዊቱ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ ጥርጊያ መንገድ መስራቱን አስታውሰዋል።
ከግድቡ ግንባታ ስኬት ጀርባም የሠራዊቱ ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን አውስተው፤ በተለይም ኮንቮይ እጀባ፣ ፈንጅ ማምከንና ጸረ-ሰላም ኃይልን በማስወገድ መስዋዕትነት መክፈሉን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አጫሉ ሸለመ፤ ባለፉት ዓመታት ሠራዊቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ለማደናቀፍ የሚሹ አካላትን ፍላጎት በማክሸፍ በደም የከበረና በታሪክ የሚታወስ የህይወት መስዋዕትነት መክፈሉን ተናግረዋል።
የሕዳሴ ግድብ ስኬትም ለሠራዊቱ አባላት ድርብ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት ማግስት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለመከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች የሰጡት ሹመት ድርብ ድል መሆኑን የሠራዊቱ ጄኔራል መኮንኖች አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ትብብር ውጤት የሆነው የሕዳሴ ግድብ ለሀገር ዕድገት መነሻ፣ የመታደስና የመለወጥ ብስራት ህያው የድል ሃውልት መሆኑንም አብራርተዋል።
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD