ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ግልጽ እና ምሳሌ የሚሆን የኑክሌር ፕሮግራም ማልማት ግቧ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሩሲያ እየተካሄደ ባለው የዓለም አቀፉ አቶሚክ ፎረም ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም፤ የኒውክሌር ኃይል በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በኢንዱስትሪ እና በፈጠራ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣቶቻችን ንቁ ናቸው፣ ከተሞቻችን እየዘመኑ ነው፣ ኢንዱስትሪዎቻችን እያደጉ ናቸው፤ ኢኮኖሚያችንም በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ካሉት መካከል አንዱ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማቷ በርካታ ዓመታትን ተጉዛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቁርጠኝነታችን ምልክት ሆኗል ብለዋል፡፡
ራዕያችን ግን ከዛሬ ባለፈ ለነገም አገራችንን የመቀየር ነው ሲሉ አንስተዋል።
የኒውክሌር ቴክኖሎጂ ዕድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂውን በኃላፊነት፣ በጥንቃቄ በማቀድ፣ ከፍተኛ የደህንነት ደረጃዎችን በማሟላት እና ጠንካራ የውስጥ አቅምን በመገንባት ለማሳካት ማቀዷንም ተናግረዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#ebc #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #PMOEthiopia #World_Atomic_Week