ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓለም አቀፉ አቶሚክ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኒውክለር ቴክኖሎጂ አስተማማኝ ኃይል ለመፍጠር እና ለጠንካራ ደህንነት እንዲሁም የውኃ አጠቃቀምን ምቹ ለማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ሩሲያ ሳይንስ ከራዕይ ጋር ሲጣመር ምን ማሳካት እንደሚችል ለዓለም አሳይታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፤ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያለውን አጋርነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
የሩሲያን ልምድ ከሰለጠነ የሰው ኃይላችን እና እያደገ ካለው ገቢያችን ጋር በማጣመር ሀገራችንን እና አህጉራችንን የሚያነቃቃ የትብብር ሞዴል ለመፍጠር ፍላጎት አለን ሲሉም ተናግረዋል።
የኒውክሌር ኃይል የረጅም ጊዜ ልማትን ለማስጠበቅ፣ የኃይል ምንጮችን ለማብዛት እና የኢትዮጵያን አቅም ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂው ሌላ ጊዜ መጠበቅ አትችልም ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይልን በሰላማዊ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት በጥንቃቄ ለመጠቀም መዘጋጀቷን ገልፀዋል።
የኒውክሌር ኃይል ሉዓላዊነታችንን የሚያጠናክርበት፣ እድገታችንን የሚደግፍበት እና ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያገለግልበትን የወደፊት ጊዜ እየነደፍን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አንድ ላይ ሆነን ምኞትን ወደ ስኬት፣ ተግዳሮቶችን ወደ ዕድሎች መለወጥ እንችላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ምስጋና አቅርበዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#ebc #ebcdotstream #AbiyAhmedAli #PMOEthiopia #World_Atomic_Week