የመስቀል በዓል ሲደርስ ምድሩም በአደይ አበባ ሲፈካ በትግራይ አዲግራት ልዩ ድባብ ያለው የበዓሉ አከባበር ይከናወናል።
ወቅቱ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች የሚገዝፉበት መሆኑን የአካባቢው ተወላጆች ያስረዳሉ።
“ለመስቀል ድርብ ከበሮ ያዙልኝ፤ ደመቅ እንዲልልኝ” እያሉ ሴቶች ያዜማሉ።
ከበዓሉ ጋር ተያይዞ “አሆሃይ” የተሰኘው ባህላዊ ትውፊት መከናወኑንም የአዲግራት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አስተባባሪ ሒወት ብርሃነ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
“አሆሃይ” የከተማ እና የገጠሩ ነዋሪ ከብቶቹን ይዞ ቅቤ እና ማር እንዲሁም ወተት ይዞ እየተመሰጋገነ የሚያሳልፈው ትውፊት መሆኑን ነው የተናገሩት።
“ሶላ” የተሰኘው በእሳት በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተጠበሰ ሥጋም ይቀርባል፤ ይህ ተወዳጅ ምግብ በተለይ በገጠራማ የአዲግራት አካባቢዎች እንደሚቀርብም የአካባቢው ተወላጆች ያነሣሉ።
በወተት እና በማባያ ቀይ ወጥ የሚቀርበው ጥህሎ፣ በተለያዩ የሥጋ ዓይነቶች የሚዘጋጀው “ግዕዝም” የተሰኘው ባህላዊ ምግብ፣ ገንፎ፣ በለስ እንዲሁም ጠጅ እና ጠላ ለበዓሉ ከሚዘጋጁት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
በዓሉ መስከረም 16 ቀን ደመቅ ብሎ ይከበራል፤ ወጣቶች “ሆያ ሆዬ” እያሉ “ቃንዳዕሮ” ከተሰኘው ተራራማ ቦታ ተነሥተው በሆታ እየዘመሩ ወደ ከተማዋ ይወርዳሉ።
የጎዳና ላይ ትርዒቶች፣ ባህላዊ ጭፈራዎች እስከ ሌሊት ይዘልቃሉ።
በዓሉ ሲከበር፤ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቶቹ በሀገር ባህል ልብስ በደመቁ ነዋሪዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ይላሉ የአካባቢው ተወላጆች።
ለዘንድሮው በዓል አዲግራት ላይ ስፖርታዊ እና ባህላዊ ፌስቲቫሎች መዘጋጀታቸውንም የተናገሩት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አስተባባሪዋ፤ የብስክሌት ውድድር፣ የዳገት ላይ ታላቁ ሩጫ እና የከተማዋን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት የሚያስችሉ የተለያዩ መሰናዶዎችም መዘጋጀታቸውንም ነው ያስረዱት።
ለበዓሉ የተለያዩ ዳያስፖራዎች፣ የስፖርት ተሳታፊዎች እና ጎብኚዎች ወደከተማዋ መግባታቸውን እና የተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች እየቀረቡ መሆኑም ታውቋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#EBC #ebcdotstream #Landoforigin #tourism #Adigirat #meskel