Search

የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ

ዓርብ መስከረም 16, 2018 76

በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዲናኦል ጫላ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ባለፈው የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ወስደው ወደ ዩኒቨርስቲ ለመግባት ማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች፣ ከካቻምናው ጭማሪ ማሳየታቸውን አቶ ዲናኦል ጫላ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቅሰዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች ማለፊያ ነጥብ ያመጡት 21 በመቶ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ባለፈው የትምህርት ዘመን ግን 30 በመቶ የሚሆኑት ማለፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አሁንም ውጤቱ በቂ አይደለም ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ በተለይ አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ዝቅተኛ ውጤት ያመጡባቸው የትምህርት አይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ይህን ለማሻሻል መሰራቱን አንስተዋል፡፡
ለዚህም የተማሪዎች፣ የመምህራን እና የወላጆች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በሥራው ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወስዱ በማድረግ የማብቃት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡
የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ሂደት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት ሌላኛው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህንን በጊዜ ሂደት ማሳካት ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ነው ያሉት፡፡
በሀገሪቱ በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች 8.4 በመቶው ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወሳል፡፡
በሜሮን ንብረት