ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በየዓመቱ ከ20 በመቶ በላይ እያደገ ላለው የኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንት ታየ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ተግባራዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢንቴቤ የተመሰረተው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ይህም በተፋሰሱ ሀገራት ትብብር የተገኘ ታላቅ ውጤት መሆኑን በተመድ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአዲስ ዓመቷ ዋዜማ ታዳሽ ኃይል የማመንጨት አቅሟን ከፍ የሚያደርግ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመርቃለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህም ለኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ተናግረዋል።
ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለሁሉም ለማዳረስ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የሥራው እውነተኛ ትርጉም በሚለውጠው የኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ታዳሽ ኃይል ለማያገኙ 60 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ብርሃን እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ግድቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ከማገዶ የሚገላግላቸው የነፃታቸው ምልክት ነው ሲሉም ፕሬዚዳንት ታየ ተናግረዋል።
"ሕዳሴ ሁሉንም ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ትልቅ ሚና ይኖረዋል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ "ሥር በሰደደ ችግር ውስጥ ለሚኖረው ሕዝባችን ንፁህ ውኃ የማቅረብ፣ ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድል የመፍጠር እና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ አቅማችንን ያሳድጋል" ብለዋል።
ግድቡ ቀጣናዊ ትስስርንም እንደሚያሻሽል አንስተዋል።
“በሕዳሴ ምርቃቱ ወቅት የተገኘው ከፍተኛ ድጋፍ እና አብሮነትም በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገሮች መካከል ትብብርን ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን ማሳያ ነው" ብለዋል።
በለሚ ታደሰ