Search

ኢትዮጵያውያን ለፈተናዎች ሳይበገሩ በራሳቸው አቅም ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቃቸው ትልቅ ትርጉም አለው - አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን

ቅዳሜ መስከረም 17, 2018 66

ኢትዮጵያውያን ለፈተናዎች እና ለችግሮች ሳይበገሩ በራሳቸው ፋይናንስ እና ጉልበት ሕዳሴ ግድብን ገንብተው ማጠናቀቃቸው ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ እና ፀሐፊ አን ጋሪሰን ገለጸች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካን የሚቀይር እና ቀጣናዊ ትስስርን የበለጠ የሚያጠናክር ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግራለች፡፡

ጋዜጠኛ አን ጋሪሰን ከኢዜአ ጋር ባደረገችው ቆይታ፤ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ እጅጉን መደሰቷን ገልጻለች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዓለማችን ላይ ዜጎች የውጭ እርዳታን ሳይጠብቁ በራሳቸው ጥሪት ከገነቧቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ሆኖ የሚጠቀስ መሆኑንም ገልጻለች።

ግድቡ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ በመቀየር፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍን በማሳደግ እና የኢኮኖሚ እድገትን በማሳለጥ ረገድ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ነው የጠቀሰችው።

ሕዳሴ አፍሪካ ያለባትን የኢነርጂን እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይር የገለጸችው ጋዜጠኛዋ ይህም ለኢኮኖሚ እድገት እና ቀጣናዊ ትስስር እንዲሳለጥ ያደርጋል ብላለች።

ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካ ሀገራት ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ለሚያደርጉት ሽግግር በምሳሌነት የሚጠቀስ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጻለች።

ግድቡ የታዳሽ ኃይል ምንጭ መሆኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እና እድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ተናግራለች።

ኢትዮጵያ በውሃ ሀብቷ ተጠቅማ የመልማት መብት አላት ያለችው ጋዜጠኛ አን በናይል ዋንዝ አብዛኛው ድርሻ ያላት ሀገር በሀብቷ የመጠቀሟ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ብላለች።

የቀጣናው እና የአፍሪካ ሀገራት ውሃን ጨምሮ ሌሎች ሀብቶቻቸውን በትብብር መንፈስ በመጠቀም የጋራ ልማት እና እድገታቸውን እንዲያረጋግጡም አመላክታለች።

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD